ጃዋር
መሐመድ ለምርጫ እንደሚወዳደር መወራት ጀምሯል፡፡ ይህ እጅግ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡
አለኝ የሚለውን ሃሣብ በሕዝብ ይሁንታ ተግባራዊ ማድረጊያ መንገድ ሰለሆነ፣ አድናቆታኝ የላቀ ነው፡፡ እራሱንም ከአክቲቪስተነት ከፍ
ማድረጉ ጥሩ ጅምር ነው፡፡ የሚያሳዝነው አቶ በቀለ ገርባን ከፖለቲከኝነት አውርዶ አክቲቪሰት ካደረገው በኋላ መሆኑ ነው፡፡ ይህ
በፖለቲካ የመሳተፍ የጃዋር ውሳኔ የሚከተሉት እንደምታዎች አሉት፤
አስደማሚው ነገር፤ ጃዋር ፖለቲካ
ውስጥ መግባቱና ለፖለቲካ ሥልጣን ለመወዳደር መወሰኑ ሳይሆን ምርጫ የምንሳተፈው እና ምርጫ የሚባል ነገር የሚኖረው በሥልጣን ክፍፍል
ከተደራደርን በኋላ ነው፤ የሚለው ትዕቢት የተሞላው አነጋገር ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ምርጫ የሚባለው ነገር እኮ ምን ያህል
ሥልጣን እንደሚኖር መወሰኛ ሥርዓት ነው፡፡ ምርጫ ማለት ፕ/ር መረራ ጉዲና ከወጣትነቱ ጀምሮ ሲጮኽለት የነበረው “የአንድ ሰው አንድ
ድምፅ” መርዕ መተግበሪያ ነው፡፡ ይህ ታልፉ ማን ምን አንደሚያገኝ ቀደሞ ተደራድሮ መወሰን ምን ማለት ነው? ሥልጣን በድርድር ከተወሰነ፤
የምርጫ ፋያዳው ምንድነው?
ለማንኛውም ጃዋር ዳግማዊ መለስ
ዜናዊ ለመሆን እየፈለገ ነው፡፡ መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያዊያን ላይ የሰራው ግፍ በቀጥታ የሕዝብ ምርጫ ሥልጣን እንደማያስገኝለት በተረዳ
ጊዜ በድርጅታዊ መንገድ ሥልጣን መያዣን የፓርላሜንተራዊ ሥርዓት በማደረግ ከሃያ ዓመት በላይ በሥልጣን መቆየት ችሏል፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያዊያን
መሪዎችን በቀጥታ የማይመርጡበት የሕግ መንግሥት ቅርቃር ውስጥ እንገኛለን፡፡ ከዚህ እስር ለመሻገር የሕገ መንግሥት ቅያሬ በሕዝብ
ይሁንታ ዳዴ በምንልበት ወቅት ሌላ ችግር ፈጣሪ ብቅ ብሏል፡፡ ዛሬም ጃዋር መሐመድ የብሔር አደረጃጀት መቀጠል አለበት፣ በዚህ ውስጥም
በቁጥራችን ልክ ሥልጣን ድርድር አድርገን ከተስማማን በኋላ ወደ ምርጫ እንግባ የሚል ቀመር ይዞ መጥቷል፡፡ ለለውጥ ተጠቀምኩበት
ያለው “ካልኩሌተር” መበላሸቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ቀድሞም ከነበር ማለት ነው፡፡ በቅርቡ የሚያገኛቸውን የኦሮሞ ፖለቲከኞች በፍፁም
ሰለናቃቸው ወይም ደግሞ በሚፈለገው ልክ ሊላላኩት ስለአልቻሉ ወደ ፖለቲካ ተሳታፎ ማደግ ፈልጓል፡፡ ይህን ንቀቱን ለመረዳት ነብይ
መሆን አያስፈልግም፡፡ በቅርቡ በሚዲያ ቀርቦ የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በግል እያገኘ የፈለገውን እንዲያሰፈፅሙ ቢልካቸውም
ከእርሱ ሃሣብ ውጭ የሚሰሩ መሆኑ በጣም እየተበሳጫ ሲናገር ነበር፡፡ ሰለዚህ ፖለቲካ ውስጥ መግባት አማራጭ የሌለው ውሣኔ ሆኖበታል፡፡
ይህ ደግሞ የውጭ ዜግነት መተውን ግድ ሰለሚል ቀድሞ ምን ቦታ እንደሚሰጡት አረጋግጦ፤ የዜግነት መልቀቅ ውሳኔ ለማድረግ የፈለገ
ይመስላል፡፡
በለውጡ ማግስት ምርጫ መኖር አለበት
ሲል የነበረ ሰውዬ፤ አሁን ደርሶ ምርጫ የሚባል ነገር አይታሰብም፤ የሚለው ለራሱ ዝግጅት ሲል መሆኑን መረዳት አያስቸግርም፡፡ ለማንኛውም
ዜግነት በቃኝ ለማለት ብዙ ደጅ መጥናት ሰለሌለው በአጭሩ የሚያልቅ ጉዳይ ነው፡፡ በዜግነቱ ያለበትን ግዴታ በአግባቡ ከተወጣ እና
የሚወራበት የታክስ ስወራ ወንጀል ካለገደው በስተቀር፣ በቶሎ አጠናቆ ወደ ፓርቲው ምሥረታ ይገባል፡፡ በእኔ እምነት በየትኞቹም የኦሮሞ
ፓርቲዎች ውስጥ ሊሳተፍ አይችልም፡፡ በተለይ በዶክተር አብይ ኦዴፓና በፕ/ር መረራ ኦፌኮ ቦታ አያገኝም፡፡ ከሁለቱም ፓርቲዎች ግን
ሰው ሊያገኝ ይችላል፡፡ በቀለ ገርባ ቀዳሚ ዕጩ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያዊ ዜግነት ካገኘ፤ ጃዋር
ምርጫ ውድድር ቢገባ እጅግ ደስ ከሚላቸው ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ መንግሥት ከፈለገ በሕግ ዜግነት የሚያስከለክል ባይኖርም በአስተዳደር
ለምርጫው እንዳይደርስ ማድረግ የሚችሉበት ተንኮል መስራት አያቅታቸውም፡፡ ለትንሽ ጊዜም ቢሆን ፓስፖርት አልባ ሰው ማድረግ ይችላሉ፡፡
ወደ ፖለቲካው ሜዳ በግልጫ ሲመጣ፤ በፌስ ቡክ ወሬ እና በተግባር ሜዳ ላይ ጫወታው ምን እንደሚመስል እናየዋለን፡፡ ጃዋር በአንድ
ምርጫ ክልል ሊመረጥ እንደሚችል ጥርጥር የለኝም፡፡ ከዚያ አልፎ መንግስት ሊያደርገው የሚያስችለው ስብስብ ይዞ መጥቶ ካሸነፈ መንግስት
ቢሆንም ችግር የለብኝም፡፡ የክልልም ቢሆን፤ ይህ ግን ቀድሞ የሚመረጥ ጉዳይ ነው፡፡
ጃዋር በእርግጠኝነት ኢትዮጵያዊያን
መሪዎችን በቀጥታ የሚመርጡበት ምርጫ እንዲኖር በፍፁም አይታገልም፡፡ ምክንያቱም የጃዋር ትግል የግል ፍላጎትና ጥቅም እንጂ የዜጎች
ሉዓላዊነት እና የሥልጣን ባለቤትነት በቀጥታ መረጋገጥ አይደለም፡፡ ጃዋር ዜጎች በቀጥታ መሪ መምረጥ አለባቸው ብሎ ሕገ መንግሥቱ
በዚህ መሰረት እንዲሻሻል ፍላጎት ሊያሳይ አይችልም፡፡ ምክንያቱም በምንም ሁኔታ በመላው ኢትዮጵያዊ ዘንድ አስተባባሪ መሪ ሊሆን
አይችልም፡፡ የዚህ ዓይነት ስብዕና ያላቸውን እንደ ዶር አብይ አህመድ ያሉትን የኦሮሞ ልጆች ለማደናቀፍ የሚሞክረው በግል ጥቅምና
ፍላጎት በመነዳት ነው፡፡
ለማንኛውም ጃዋር የምር ከሆነ እንኳ
ወደ ፖለቲካ ሰፈራችን መጣህ ለማለት እወዳለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment