Monday, July 29, 2019

መጥረጊያና ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ….



ጠቅላይ ሚኒሰትር አብይ አህመድ መጥረጊያ ይዘው በየወሩ ለፅዳት መውጣት፤ ብሎም ከቆሻሻው ማፅዳቱ ጋር አብረን የተበላሻ አስተሳሰብም እንፃድ፤ ሸገር እራት ብለው ለአዲስ አበባ ወንዞች የያዙት የከተማ ማስዋብ ፕሮጀክት፤  ዘወትር መስጠት ያስደስታል ማለታቸው ድጋፍም፣ ተቃውሞም እያስተናገደ ነው፡፡ በሙስሊሞች ፆም ማገባደጃ ዋዜማ ደግሞ የመስገጃ ቦታውን ለማፅዳት በማለዳ አዲስ አበባ ስታዲዮም ተገኝተው ከአንቅልፍ ስንነቃ ሌላ የሚዲያ ወሬ በመፍጠር ግርምት ፈጥረው ከርመዋል፡፡ ችግኝ ተከላ፣ የስብዓዊ አገልግሎት መሰጫ ድርጅቶች ጉብኝት፤ ቢያንስ ሳምንታዊ ክንውኖች እየሆኑ ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ ጎራ ያላ የውጭ አገር ጎብኚም ችግኝ በመተከል ተሳታፊ እንዲሆን እየተደረገ ነው፡፡  ይህን በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያ ብቻ ሳይሆን፤ በግልም የማህበራዊ ግንኙነት የመወያያ ርዕስ መሆኑ እውነት ነው፡፡ የዛሬ ፅሁፌ መነሻ ከታናሽ ወንድሜ ጋር በዚሁ ጉዳይ ቀጠሮ ይዘን ያደረግነው ሰፋ ያለ ወግ ነው፡፡
ወንድሜ በአንድ ወቅት ቦትሶዋና ዋና ከተማ ጋቦሮኒ ወጣ ብሎ በሚገኝ ደን ውስጥ የወሰደው “የምድር ሕግ” (Earth Jurisprudence) በሚል ርዕስ የተሰጠን ሥልጠና መሰረት አድርጎ ብዙ አጫወተኝ፡፡ የሥልጠናው ትኩረቱ  የአፍሪካ መሪዎች በአገራቸውን ያለውን መሰረታዊ ችግር ለመፍታት፤ ወደ ቀድሞ ነገራቸው መመለስ እና በቅኝ ግዛት ካዳበሩት ስነልቦና ተላቀው ወደ ተፈጥሮ እና አገር በቀል እውቀት መመለስ ሲችሉ ነው የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡ የአፍሪካ አንኳር ችግሮች ፍርሃት፣ ግለኝነት/ሰግብግብነት፣ ከተፈጥሮ አና ሀገር በቀል እውቀት ጋር መጣላት እና ማዕበራዊ ዕሴት መላሸቅ ናቸው ተብሎ ይታማናል፡፡ መፍትሔውም እነዚህን ክሽፈቶች ወደ ቀድሞ ነገራቸው መመለስ ነው፣ የተፈጥሮ ሕግን ማወቅ፤ ተፈጥሮ የሰጠችንን አውቆ መጠቀም የሚል ነው፡፡ ሥልጠናው የወንጀልና የፍትሓብሔር ሕግ ማስከበር ብቻውን ችግሩን አይፈታም፤ ይልቁንም ያዳፍናል የሚል እምነት ይዞ በተግባር ከተፈጥሮ ጋር አገናኝቶ የሚያስተምር ነው፡፡ እነዚህን ጉዳዮች በአጭሩ ለማየት እንሞክር፤
ፍርሃት፤
በግለሰብ ደረጃ የፍርሃት ምንጭ ጨለማ፣ ብቸኝነት፣ መገለል፣ አውሬ፣ ውሃ ሙላት፣ ሞት፣ ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለፖለቲካ መሪዎች ደግሞ ከሥልጣን ወንበራቸው መነቀል ዋንኛ የፍርሃታቸው ምንጭ ነው፡፡ ከሥልጣን ወንበራቸው ሲነቀሉም የውሻ ሞት መሞት ጭንቀት ውስጥ የሚከታቸው፣ ከዚህም ፍርሃት ለመውጣት፤ አፈናን መፍትሔ አድርጎ መውሰድ ነው፡፡ ፍርሃትን በመፍራት ወይም ደግሞ በመሽሽ ልናስወግደው አንችልም፡፡ ባለሞያዎች የሚመክሩት ፍርሃትን በዘላቂነት ማስወገጃው መንገድ፣ መጋፈጥ ነው፡፡ ለአፍሪካ መሪዎች ከተጫናቸው የፍርሃት ድባብ ለመውጣት፣ የሚፈሩትን ሕዝብ መቅረብ ወረድ ብሎ ኑሮዉን ማወቅ፣ አብሮ መኖር፣ ብቸኛው መፍትሔ ነው፡፡ በሥልጣን ማማ ላይ ሲወጡ፣ የነበሩበትን ቦታ ያለመርሳት መመላሻ ቦታ መሆኑን ጠንቅቆ መረዳት ይጠይቃል፡፡ ፕሮፌስር መስፍን እንደሚሉት የመሰላሉን መወጣጫ በእግር አለማቆሽሽ፤ ሲወርዱ በእጅ የሚያዘው መውረጃም ይሆናል የሚሉትን የሚያስታውስ ነው፡፡
በግለሰብ ደረጃ ያሉ ፍርሃቶች በልምምድ የሚወገዱ ናቸው፡፡ ጨለማ የሚፈራን ሰው፣ በጨለማ ውስጥ ቀስ በቀስ እንዲሆን አድርጎ ማለማመድ ይቻላል፡፡ ከሰዎች ጋር መግባባት ተቸግሮ እራሱን የሚያገል ወይም የሚገለል ሰው የተግባቡት ሥልጠና በመውሰድና በተግባር በመለማመድ ችግሩን ሊፈታው ይችላል፡፡ለፖለቲካ መሪዎች ከሕዝብ ተነጥለው በመኖር፤ ወደ ሕዝብ መመለስ ድቅድቅ ጨለማ ቢሆንባቸው መመለሻው መንገድ በፕሮቶኮል የታጠረ፣ የአዳራሽ ስብሰባ በፍፁም ሊሆን አይችልም፡፡ የመክፈቻና የመዝጊያ ንግግሮች ለሕዝብ ቅርበትን አያሳዩም፡፡ ግፉዋን የሚኖሩበትን ሰፈር መጎብኘት፣ ጥዩፍ የሆነውን ቆሻሻ በእጅ ማንሳት፣ አፈር ማስ ማስ አድርጎ ችግኝ መትክል ወደ ተፈጥሮ መቅረቢያው መንገድ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መጥረጊያ ይዘው ወደ ሕዝቡ የሚሄዱበት ምክንያት ይህ ገብቷቸው፤ ከተፈጥሮ ጋር እርቅ ፈጥረው እኛም እንድንፈጥር ከሆነ በእውነት መልካም ጅምር ነው፡፡ መጥሪጊያውን የሚነቅፉ ሰዎች ስተዋል ማለት ይቻላል፡፡
ግለኝነት/ስግብግብነት
በዜጎች መካከል የሚታዩ የግለኝነት ወይም የስግብግብነት ሁኔታ ምን ያህል ፈር እንደሳታ ለማወቅ ራሳችንን እንዲሁም አጠገባችን ያለውን ሁሉ መታዘብ ያስፈልጋል፡፡ ወደ ምድር ባዶዋችንን መጥተን፣ ሌጣችንን መመለሳችንን ዘንግተናል፡፡ በየከተማው የሚደረገው የመሬት ወረራ፣ ተፈጥሮን እያራቆቱ ለመብልፀግ የሚደረገው እሩጫ፣ እንዲኖረን የምንፈልገው የቁሳቁስ ዓይነትና ብዛት፣ ወዘተ ቅጥ ያጣ ስግብግብነት እና አልጠግብ ባይነታችንን የሚያሳዩ ጉልዕ ማሳያዎች ናቸው፡፡
ብዙ ሺ ሄክተር ቤተመንግስት አጥሮ ይዞ፣ በአጥሩ አትለፉ፣ ፎቶ አታንሱ፣ መኪናችሁ እዛ ሰፈር እንዳይበላሽ ማለት፤ ከስግብግብነታችን የሚመጣ ካልሆነ ከአሜሪካ ቤተ መንግሥት በተለይ ለሽብር ተጋላጭ መሆናችንን አያሳይም፡፡ ለመለስ ዜናዊ ስንብት የተከፈተው ቤተ መንግሥት በቅርቡ ለህዝብ ክፍት ይሆናል፤ ሰርግም ይደገስበታል፣ መባሉን፣ እንደ በጎ ጅምር ማየት ልንቸገር አይገባም፡፡
ስግብግብነትን ማጥፊያው መንገድ ከመስጠት የሚገኘውን ደስታ መረዳትና መተግበር ነው፡፡ ከግብሰብስብ ቁሶች ይልቅ የምንሰጣቸው የበለጠ ደስታ ፈጥረው የሰላም እንቅልፍ እንደሚቸሩን በተግባር ማሳየትና ማለማመድ ያስፈልጋል፡፡ ሹመኞች “ሲሾም ያልበላ፤ ሲሻር ይቆጨዋል፡፡” ከሚል ተፈጥሮን ከሚቃረን ብሂል እንዲፋቱ አበክረን መስራት ይኖርብናል፡፡ ሹሞች በስግብግብነት ተሰብስቦ፤ ባለጸጋ ከማያደርግ የቁስ ክምችት እንዲላቀቁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የአፍሪካ መሪዎች በምሣሌ መምራት ካለባቸው ክፍርሃት መገላገያ የሚመስላቸው ቁሳቁስ ማከማቸት፣ ወደ ፍርሃት አርንቋ የሚከታቸው እንደሆነ ሊረዱት እና ሊኖሩት ይገባል፡፡ ጠቅላይ ሚኒሰትር አብይ አህመድ በእውነት ይህን ተረድተው ለግል ቁስ እንደማይጨነቁ፣ ነግረውናል፡፡ ይልቁንም መስጠትን እየሰበኩ፣ አሻራ አኑሩ እያሉን ነው፡፡ ይህን ማመን፣ አምነንም ይህን መስበክ ይኖርብናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይታመኑ ቢቀሩ እዳው ከሳቸው አልፎ ለልጆቻቸው ይተርፋል፡፡ ያመንን እና የተገበርን ደግሞ እናተርፍበታል፡፡ ልጆቻችን ከቁስ አላቀን ከተፈጥሮ ጋር አዋደን ልናሳድግ ይገባል፡፡
 ከተፈጥሮ አና ሀገር በቀል እውቀት ጋር መጣላት
ልንጋፈጣቸው ከሚገቡን መሰረታዊ ችግሮች አንዱ የሆነው ከተፈጥሮ እና አገር በቀል እውቀቶች መጣላታችን፤ በምትኩ በምዕራብ መጤ ሽብርቅርቅ ተጠምደን መባከናቸን ነው፡፡ የተፈጥሮ ፀጋዎችን መተው ብቻ ሳይሆን፤ በዘፈቀደ ማውደም ላይ ተጠምደናል፡፡ ደን ተከላን እንቃወማለን፣ ለመፋቂያ የሚሆን እንጨት ለማግኘት ብዙ ርቀት እንጓዛለን፡፡ መፋቂያ ማዘመን ትተን፣ የጥርስ ቡርሽ ማስታወቂያ ተገዥ ሆነናል፡፡ ለውዝ፣ ኮኮናት፣ ቡና፣ የቅባት እህል፣ ወዘተ ሽጠን ቸኮሌት፣ ካፌን፣ ዘይት፣ ማስቲካ ወዘተ .. ከውጭ እናስገባለን፡፡ ተፈጥሮ የሰጠንን/ኦርጋኒክ የሚባለውን ትተን፣ በኬሚካል የተሰሩ ምርቶች አፍቃሪ ሆነናል፡፡ በከተማችን መናፈሻ አጥፍተን ፎቅ እንገነባለን፡፡ ለዚህ ሁሉ ማድረጊያ የሚስፈልገን ገንዘብ ከውጭ በብድር ጭምር እንወስዳለን፡፡ በመጨረሻ በእዳ ተዘፍቀን በዶላር እጥረት አንማስናለን፡፡
ፈረንጆቹ ከተፈጥሮ ጋር ለመታረቅ ሶፋ ላይ ከመቀመጥ፣ መሬት ላይ መሆን፣ በጫማ ከመሄድ ቢያንስ በቤታችን በእግራችን በመሆን ከተፈጥሮ ጋር መገናኘት (Ground to Earth)፣ አፈርን በእጅ መንካት፣ በአፍንጫ ማሽተት፤ ተክሎችን በጊቢያችን ማሳደግ፤ ጠቃሚ ነው ብለው ይተገብራሉ፡፡ እኛ ቢያንስ መሰረታዊ የመድሃኒትነት ባህሪ ያላቸውን (ዳማከሴ፣ ጤናዳም፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ወዘተ..) በቅጥር ጊቢያችን በቀላሉ ማግኘት፤ የሚያስችል ሁኔታ ውስጥ ሆነን፤ ከኒውክለር ፊዚክስ እኩል እንዴት ከባድ ይሆንብናል? ሚስጥሩ ዘመናዊ የሆንን መስሎን ከተፈጥሮ መጣላት፤ አገር ብቀል እውቀት መናቅ ነው፡፡ መፍትሔው ወደ ቀድሞ ነገራችን ተመልስን በጥሞና መመርመር፤ ራስን ማክበር፣ ከውጭም ቢሆን መርጦ መውስድ ነው፡፡
መፍትሔው ችግኝ በመትከል ስም ዛፍ መተከል አይደለም፡፡ አገር በቀል የሆኑት የብዝሃ ሕይወቶች መርጦ እንዳይጠፉ ብቻ ሳይሆን እንዲበዙ ማድረግና መጠቀም ነው፡፡ የማገዶ ዛፍ ብቻ ሳይሆን የሚያስፈልገን፣ በምግብ እህል እራሳችንን እንድንችል የሚያደርጉ፣ ህፃናትን ከመቀንጨር የሚጠብቁ ብዙ ተክሎችን ከዘመቻ ስሜት ወጥተን መደበኛ ሥራችን ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ጊቢያችንን ሙሉ ሴራሚክስ አድርገን፣ በእግራችን ልንንጎራደድ የምንችልበት ቦታ አይገኝም፡፡
ባለሞያዎች፤ ለሁሉም በሽታ መድሓኒቱ፤ ከውስጥ የሚመነጭ የተፈጥፎ ሀይል ነው ይላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከተፈጥሮ የሚገኝ ነው፡፡ ቻይናዎች ኽርባል ተፈጥሮዋዊ መድሐኒት በሚል ለዓለም እያቀረቡት ይገኛለ፡፡ የዘመናዊ መድሃኒቶች መሰረቱም ይህ የተፈጥሮ ስጦታ ነው፡፡ ተፈጥሮን አፍሪካ ታክብር፣ መሪዎች ይህን ያድርጉ ብለው እየመከሩን ነው፡፡ የችግኝ ተከላው ከተፈጥሮ ጋር የሚያስታርቀን እንዲሆን አስበን እንስራ፡፡
ማዕበራዊ ዕሴት መላሸቅ
ከወንድሜ ጋር በነበረን ውይይት አንዱ ትልቁ ነጥብ አፍሪካዊያን እየተውነው የመጣነው፣ የመወለድ መብት (Birth Right) ጉዳይ ነው፡፡ የመወለድ መብት ቀድሞ በመወለድ ብቻ የሚገኝ መብት ነው፡፡ ታናሽ፤ ታላቁን ማክበር፡፡ ታላቅ ለታናሹ ከለላ መሰጠት፡፡ ይህ በተፈጥሮ በሚገኝ ቀድሞ በመወለድ ብቻ የሚገኝ መብት ነው፡፡ ሌላው ወላጆች ያላቸው ሚና ነው፡፡ ወላጅ ልጅ ጭልጥ ብሎ ሲያንቀላፋ፤ የልጁን ትንፋሽ ማዳመጥ በተፈጥሮ ያለ የፍቅር ስጦታ ነው፡፡ እነዚህ በቤተሰብ የሚጀምሩ የመልካም ማዕበራዊ ግንኙነት መሰረት ናቸው፡፡ ይህን መልካም እሴት፣ በጥሰን ጥለናል፡፡ አሁን የምንፈጥረው ግንኙነት የትኛው ወንድሜ በቁስ የላቀ ነው ወደሚል ተቀይሯል፡፡ ዶላር የሚልክ፤ በውጭ የሚኖር የበለጠ “ክብር” ይሰጠዋል፡፡ ከቤተሰብ የበጠስነው እሴት፤ ታላቅን የማክበር፣ ታናሽን የመንከባከብ፣ ወላጅን መታዘዝ፤ ፤ በማሕበረሰብ ደረጃ ለአረጋዊና ሽማግሌ ክብር፣ በእድሜ ለሚገኝ ፀጋ አውቅና መስጠት ተስኖናል፡፡ ለዚህም ነው በቅርቡ በአርባ ምንጭ አካባቢ እንጥፍጣፊ የሽምግልና በጎ ምግባር ሰናይ፤ ብርቅ ሆኖብን የቦረቅነው፡፡ በቤተሰብ ደረጃ ማዕድ ከበን መቋደሱ፣ በሶፋ ላይ ወይም በቁንን የምግብ ጠረጴዛ ዙሪያ በቁርጥ እንጀራ መቀየሩ፣ በመሶብ ዙሪያ የሚገኘውን የማሕበራዊ እሴት አሳጥቶናል፡፡ ይህን ዕሴት ወደ ቀድሞ ለመመለስ እጅግ ብዙ ስራ ይጠበቅብናል፡፡ በቅድሚያ በቤታችን መከባበር፤ ቀጥሎ ጎረቤት ማክበርና ማገዝ ያስፈልገናል፡፡ ይህ ድምር ለአካባቢ ሰላም ይጠቅመናል፡፡ የጋራ ባለአገርነት ሰሜት ይፈጥርብናል፡፡
እንደ ፈረንጆቹ ዘመናዊ የማሕበራዊ ዋስትና ስርዓት ሳንዘረጋ፤ የራሳችንን በጥሰን፤ አዛውንቶችን፣ ሕፃናትን ለጎዳና ኑሮ የዳረግነው፡፡ ይህን ሊያደርጉ የሚጠበቅባቸው ቤተ እምነቶቻችን፣ የእምነት አባቶች፣ ለዚህ በጎ ምግባር ሊያሰልፉን አልቻሉም፡፡ ከእብደታችን ተገሳፅ ሰጥተው ተዉ የሚሉ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ይልቁንም እንደ ዓለማዊያን ሁሉ እነርሱም በመንግሥት እግር ሥር ወድቀው ልማታዊ ሆነው፤ ክብርም ሞገስም አጥተዋል፡፡ በቅርቡ በእምነት ተቋማት ቀድመው በውስጣቸው ያለውን ሰንኮፍ ነቅለው፤ ቶሎ ወደ ምህመኑ ይመጣሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ የዛኔ ለማህበራዊ ስብራታችን ጠጠር ያስቀምጣሉ፡፡

No comments:

Post a Comment