Friday, October 25, 2019

ጃዋር ዳግማዊ መለስ



ጃዋር መሐመድ ለምርጫ እንደሚወዳደር መወራት ጀምሯል፡፡ ይህ እጅግ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡ አለኝ የሚለውን ሃሣብ በሕዝብ ይሁንታ ተግባራዊ ማድረጊያ መንገድ ሰለሆነ፣ አድናቆታኝ የላቀ ነው፡፡ እራሱንም ከአክቲቪስተነት ከፍ ማድረጉ ጥሩ ጅምር ነው፡፡ የሚያሳዝነው አቶ በቀለ ገርባን ከፖለቲከኝነት አውርዶ አክቲቪሰት ካደረገው በኋላ መሆኑ ነው፡፡ ይህ በፖለቲካ የመሳተፍ የጃዋር ውሳኔ የሚከተሉት እንደምታዎች አሉት፤
አስደማሚው ነገር፤ ጃዋር ፖለቲካ ውስጥ መግባቱና ለፖለቲካ ሥልጣን ለመወዳደር መወሰኑ ሳይሆን ምርጫ የምንሳተፈው እና ምርጫ የሚባል ነገር የሚኖረው በሥልጣን ክፍፍል ከተደራደርን በኋላ ነው፤ የሚለው ትዕቢት የተሞላው አነጋገር ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ምርጫ የሚባለው ነገር እኮ ምን ያህል ሥልጣን እንደሚኖር መወሰኛ ሥርዓት ነው፡፡ ምርጫ ማለት ፕ/ር መረራ ጉዲና ከወጣትነቱ ጀምሮ ሲጮኽለት የነበረው “የአንድ ሰው አንድ ድምፅ” መርዕ መተግበሪያ ነው፡፡ ይህ ታልፉ ማን ምን አንደሚያገኝ ቀደሞ ተደራድሮ መወሰን ምን ማለት ነው? ሥልጣን በድርድር ከተወሰነ፤ የምርጫ ፋያዳው ምንድነው?
ለማንኛውም ጃዋር ዳግማዊ መለስ ዜናዊ ለመሆን እየፈለገ ነው፡፡ መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያዊያን ላይ የሰራው ግፍ በቀጥታ የሕዝብ ምርጫ ሥልጣን እንደማያስገኝለት በተረዳ ጊዜ በድርጅታዊ መንገድ ሥልጣን መያዣን የፓርላሜንተራዊ ሥርዓት በማደረግ ከሃያ ዓመት በላይ በሥልጣን መቆየት ችሏል፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያዊያን መሪዎችን በቀጥታ የማይመርጡበት የሕግ መንግሥት ቅርቃር ውስጥ እንገኛለን፡፡ ከዚህ እስር ለመሻገር የሕገ መንግሥት ቅያሬ በሕዝብ ይሁንታ ዳዴ በምንልበት ወቅት ሌላ ችግር ፈጣሪ ብቅ ብሏል፡፡ ዛሬም ጃዋር መሐመድ የብሔር አደረጃጀት መቀጠል አለበት፣ በዚህ ውስጥም በቁጥራችን ልክ ሥልጣን ድርድር አድርገን ከተስማማን በኋላ ወደ ምርጫ እንግባ የሚል ቀመር ይዞ መጥቷል፡፡ ለለውጥ ተጠቀምኩበት ያለው “ካልኩሌተር” መበላሸቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ቀድሞም ከነበር ማለት ነው፡፡ በቅርቡ የሚያገኛቸውን የኦሮሞ ፖለቲከኞች በፍፁም ሰለናቃቸው ወይም ደግሞ በሚፈለገው ልክ ሊላላኩት ስለአልቻሉ ወደ ፖለቲካ ተሳታፎ ማደግ ፈልጓል፡፡ ይህን ንቀቱን ለመረዳት ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡ በቅርቡ በሚዲያ ቀርቦ የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በግል እያገኘ የፈለገውን እንዲያሰፈፅሙ ቢልካቸውም ከእርሱ ሃሣብ ውጭ የሚሰሩ መሆኑ በጣም እየተበሳጫ ሲናገር ነበር፡፡ ሰለዚህ ፖለቲካ ውስጥ መግባት አማራጭ የሌለው ውሣኔ ሆኖበታል፡፡ ይህ ደግሞ የውጭ ዜግነት መተውን ግድ ሰለሚል ቀድሞ ምን ቦታ እንደሚሰጡት አረጋግጦ፤ የዜግነት መልቀቅ ውሳኔ ለማድረግ የፈለገ ይመስላል፡፡
በለውጡ ማግስት ምርጫ መኖር አለበት ሲል የነበረ ሰውዬ፤ አሁን ደርሶ ምርጫ የሚባል ነገር አይታሰብም፤ የሚለው ለራሱ ዝግጅት ሲል መሆኑን መረዳት አያስቸግርም፡፡ ለማንኛውም ዜግነት በቃኝ ለማለት ብዙ ደጅ መጥናት ሰለሌለው በአጭሩ የሚያልቅ ጉዳይ ነው፡፡ በዜግነቱ ያለበትን ግዴታ በአግባቡ ከተወጣ እና የሚወራበት የታክስ ስወራ ወንጀል ካለገደው በስተቀር፣ በቶሎ አጠናቆ ወደ ፓርቲው ምሥረታ ይገባል፡፡ በእኔ እምነት በየትኞቹም የኦሮሞ ፓርቲዎች ውስጥ ሊሳተፍ አይችልም፡፡ በተለይ በዶክተር አብይ ኦዴፓና በፕ/ር መረራ ኦፌኮ ቦታ አያገኝም፡፡ ከሁለቱም ፓርቲዎች ግን ሰው ሊያገኝ ይችላል፡፡ በቀለ ገርባ ቀዳሚ ዕጩ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያዊ ዜግነት ካገኘ፤ ጃዋር ምርጫ ውድድር ቢገባ እጅግ ደስ ከሚላቸው ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ መንግሥት ከፈለገ በሕግ ዜግነት የሚያስከለክል ባይኖርም በአስተዳደር ለምርጫው እንዳይደርስ ማድረግ የሚችሉበት ተንኮል መስራት አያቅታቸውም፡፡ ለትንሽ ጊዜም ቢሆን ፓስፖርት አልባ ሰው ማድረግ ይችላሉ፡፡ ወደ ፖለቲካው ሜዳ በግልጫ ሲመጣ፤ በፌስ ቡክ ወሬ እና በተግባር ሜዳ ላይ ጫወታው ምን እንደሚመስል እናየዋለን፡፡ ጃዋር በአንድ ምርጫ ክልል ሊመረጥ እንደሚችል ጥርጥር የለኝም፡፡ ከዚያ አልፎ መንግስት ሊያደርገው የሚያስችለው ስብስብ ይዞ መጥቶ ካሸነፈ መንግስት ቢሆንም ችግር የለብኝም፡፡ የክልልም ቢሆን፤ ይህ ግን ቀድሞ የሚመረጥ ጉዳይ ነው፡፡
ጃዋር በእርግጠኝነት ኢትዮጵያዊያን መሪዎችን በቀጥታ የሚመርጡበት ምርጫ እንዲኖር በፍፁም አይታገልም፡፡ ምክንያቱም የጃዋር ትግል የግል ፍላጎትና ጥቅም እንጂ የዜጎች ሉዓላዊነት እና የሥልጣን ባለቤትነት በቀጥታ መረጋገጥ አይደለም፡፡ ጃዋር ዜጎች በቀጥታ መሪ መምረጥ አለባቸው ብሎ ሕገ መንግሥቱ በዚህ መሰረት እንዲሻሻል ፍላጎት ሊያሳይ አይችልም፡፡ ምክንያቱም በምንም ሁኔታ በመላው ኢትዮጵያዊ ዘንድ አስተባባሪ መሪ ሊሆን አይችልም፡፡ የዚህ ዓይነት ስብዕና ያላቸውን እንደ ዶር አብይ አህመድ ያሉትን የኦሮሞ ልጆች ለማደናቀፍ የሚሞክረው በግል ጥቅምና ፍላጎት በመነዳት ነው፡፡
ለማንኛውም ጃዋር የምር ከሆነ እንኳ ወደ ፖለቲካ ሰፈራችን መጣህ ለማለት እወዳለሁ፡፡

Monday, July 29, 2019

መጥረጊያና ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ….



ጠቅላይ ሚኒሰትር አብይ አህመድ መጥረጊያ ይዘው በየወሩ ለፅዳት መውጣት፤ ብሎም ከቆሻሻው ማፅዳቱ ጋር አብረን የተበላሻ አስተሳሰብም እንፃድ፤ ሸገር እራት ብለው ለአዲስ አበባ ወንዞች የያዙት የከተማ ማስዋብ ፕሮጀክት፤  ዘወትር መስጠት ያስደስታል ማለታቸው ድጋፍም፣ ተቃውሞም እያስተናገደ ነው፡፡ በሙስሊሞች ፆም ማገባደጃ ዋዜማ ደግሞ የመስገጃ ቦታውን ለማፅዳት በማለዳ አዲስ አበባ ስታዲዮም ተገኝተው ከአንቅልፍ ስንነቃ ሌላ የሚዲያ ወሬ በመፍጠር ግርምት ፈጥረው ከርመዋል፡፡ ችግኝ ተከላ፣ የስብዓዊ አገልግሎት መሰጫ ድርጅቶች ጉብኝት፤ ቢያንስ ሳምንታዊ ክንውኖች እየሆኑ ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ ጎራ ያላ የውጭ አገር ጎብኚም ችግኝ በመተከል ተሳታፊ እንዲሆን እየተደረገ ነው፡፡  ይህን በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያ ብቻ ሳይሆን፤ በግልም የማህበራዊ ግንኙነት የመወያያ ርዕስ መሆኑ እውነት ነው፡፡ የዛሬ ፅሁፌ መነሻ ከታናሽ ወንድሜ ጋር በዚሁ ጉዳይ ቀጠሮ ይዘን ያደረግነው ሰፋ ያለ ወግ ነው፡፡
ወንድሜ በአንድ ወቅት ቦትሶዋና ዋና ከተማ ጋቦሮኒ ወጣ ብሎ በሚገኝ ደን ውስጥ የወሰደው “የምድር ሕግ” (Earth Jurisprudence) በሚል ርዕስ የተሰጠን ሥልጠና መሰረት አድርጎ ብዙ አጫወተኝ፡፡ የሥልጠናው ትኩረቱ  የአፍሪካ መሪዎች በአገራቸውን ያለውን መሰረታዊ ችግር ለመፍታት፤ ወደ ቀድሞ ነገራቸው መመለስ እና በቅኝ ግዛት ካዳበሩት ስነልቦና ተላቀው ወደ ተፈጥሮ እና አገር በቀል እውቀት መመለስ ሲችሉ ነው የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡ የአፍሪካ አንኳር ችግሮች ፍርሃት፣ ግለኝነት/ሰግብግብነት፣ ከተፈጥሮ አና ሀገር በቀል እውቀት ጋር መጣላት እና ማዕበራዊ ዕሴት መላሸቅ ናቸው ተብሎ ይታማናል፡፡ መፍትሔውም እነዚህን ክሽፈቶች ወደ ቀድሞ ነገራቸው መመለስ ነው፣ የተፈጥሮ ሕግን ማወቅ፤ ተፈጥሮ የሰጠችንን አውቆ መጠቀም የሚል ነው፡፡ ሥልጠናው የወንጀልና የፍትሓብሔር ሕግ ማስከበር ብቻውን ችግሩን አይፈታም፤ ይልቁንም ያዳፍናል የሚል እምነት ይዞ በተግባር ከተፈጥሮ ጋር አገናኝቶ የሚያስተምር ነው፡፡ እነዚህን ጉዳዮች በአጭሩ ለማየት እንሞክር፤
ፍርሃት፤
በግለሰብ ደረጃ የፍርሃት ምንጭ ጨለማ፣ ብቸኝነት፣ መገለል፣ አውሬ፣ ውሃ ሙላት፣ ሞት፣ ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለፖለቲካ መሪዎች ደግሞ ከሥልጣን ወንበራቸው መነቀል ዋንኛ የፍርሃታቸው ምንጭ ነው፡፡ ከሥልጣን ወንበራቸው ሲነቀሉም የውሻ ሞት መሞት ጭንቀት ውስጥ የሚከታቸው፣ ከዚህም ፍርሃት ለመውጣት፤ አፈናን መፍትሔ አድርጎ መውሰድ ነው፡፡ ፍርሃትን በመፍራት ወይም ደግሞ በመሽሽ ልናስወግደው አንችልም፡፡ ባለሞያዎች የሚመክሩት ፍርሃትን በዘላቂነት ማስወገጃው መንገድ፣ መጋፈጥ ነው፡፡ ለአፍሪካ መሪዎች ከተጫናቸው የፍርሃት ድባብ ለመውጣት፣ የሚፈሩትን ሕዝብ መቅረብ ወረድ ብሎ ኑሮዉን ማወቅ፣ አብሮ መኖር፣ ብቸኛው መፍትሔ ነው፡፡ በሥልጣን ማማ ላይ ሲወጡ፣ የነበሩበትን ቦታ ያለመርሳት መመላሻ ቦታ መሆኑን ጠንቅቆ መረዳት ይጠይቃል፡፡ ፕሮፌስር መስፍን እንደሚሉት የመሰላሉን መወጣጫ በእግር አለማቆሽሽ፤ ሲወርዱ በእጅ የሚያዘው መውረጃም ይሆናል የሚሉትን የሚያስታውስ ነው፡፡
በግለሰብ ደረጃ ያሉ ፍርሃቶች በልምምድ የሚወገዱ ናቸው፡፡ ጨለማ የሚፈራን ሰው፣ በጨለማ ውስጥ ቀስ በቀስ እንዲሆን አድርጎ ማለማመድ ይቻላል፡፡ ከሰዎች ጋር መግባባት ተቸግሮ እራሱን የሚያገል ወይም የሚገለል ሰው የተግባቡት ሥልጠና በመውሰድና በተግባር በመለማመድ ችግሩን ሊፈታው ይችላል፡፡ለፖለቲካ መሪዎች ከሕዝብ ተነጥለው በመኖር፤ ወደ ሕዝብ መመለስ ድቅድቅ ጨለማ ቢሆንባቸው መመለሻው መንገድ በፕሮቶኮል የታጠረ፣ የአዳራሽ ስብሰባ በፍፁም ሊሆን አይችልም፡፡ የመክፈቻና የመዝጊያ ንግግሮች ለሕዝብ ቅርበትን አያሳዩም፡፡ ግፉዋን የሚኖሩበትን ሰፈር መጎብኘት፣ ጥዩፍ የሆነውን ቆሻሻ በእጅ ማንሳት፣ አፈር ማስ ማስ አድርጎ ችግኝ መትክል ወደ ተፈጥሮ መቅረቢያው መንገድ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መጥረጊያ ይዘው ወደ ሕዝቡ የሚሄዱበት ምክንያት ይህ ገብቷቸው፤ ከተፈጥሮ ጋር እርቅ ፈጥረው እኛም እንድንፈጥር ከሆነ በእውነት መልካም ጅምር ነው፡፡ መጥሪጊያውን የሚነቅፉ ሰዎች ስተዋል ማለት ይቻላል፡፡
ግለኝነት/ስግብግብነት
በዜጎች መካከል የሚታዩ የግለኝነት ወይም የስግብግብነት ሁኔታ ምን ያህል ፈር እንደሳታ ለማወቅ ራሳችንን እንዲሁም አጠገባችን ያለውን ሁሉ መታዘብ ያስፈልጋል፡፡ ወደ ምድር ባዶዋችንን መጥተን፣ ሌጣችንን መመለሳችንን ዘንግተናል፡፡ በየከተማው የሚደረገው የመሬት ወረራ፣ ተፈጥሮን እያራቆቱ ለመብልፀግ የሚደረገው እሩጫ፣ እንዲኖረን የምንፈልገው የቁሳቁስ ዓይነትና ብዛት፣ ወዘተ ቅጥ ያጣ ስግብግብነት እና አልጠግብ ባይነታችንን የሚያሳዩ ጉልዕ ማሳያዎች ናቸው፡፡
ብዙ ሺ ሄክተር ቤተመንግስት አጥሮ ይዞ፣ በአጥሩ አትለፉ፣ ፎቶ አታንሱ፣ መኪናችሁ እዛ ሰፈር እንዳይበላሽ ማለት፤ ከስግብግብነታችን የሚመጣ ካልሆነ ከአሜሪካ ቤተ መንግሥት በተለይ ለሽብር ተጋላጭ መሆናችንን አያሳይም፡፡ ለመለስ ዜናዊ ስንብት የተከፈተው ቤተ መንግሥት በቅርቡ ለህዝብ ክፍት ይሆናል፤ ሰርግም ይደገስበታል፣ መባሉን፣ እንደ በጎ ጅምር ማየት ልንቸገር አይገባም፡፡
ስግብግብነትን ማጥፊያው መንገድ ከመስጠት የሚገኘውን ደስታ መረዳትና መተግበር ነው፡፡ ከግብሰብስብ ቁሶች ይልቅ የምንሰጣቸው የበለጠ ደስታ ፈጥረው የሰላም እንቅልፍ እንደሚቸሩን በተግባር ማሳየትና ማለማመድ ያስፈልጋል፡፡ ሹመኞች “ሲሾም ያልበላ፤ ሲሻር ይቆጨዋል፡፡” ከሚል ተፈጥሮን ከሚቃረን ብሂል እንዲፋቱ አበክረን መስራት ይኖርብናል፡፡ ሹሞች በስግብግብነት ተሰብስቦ፤ ባለጸጋ ከማያደርግ የቁስ ክምችት እንዲላቀቁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የአፍሪካ መሪዎች በምሣሌ መምራት ካለባቸው ክፍርሃት መገላገያ የሚመስላቸው ቁሳቁስ ማከማቸት፣ ወደ ፍርሃት አርንቋ የሚከታቸው እንደሆነ ሊረዱት እና ሊኖሩት ይገባል፡፡ ጠቅላይ ሚኒሰትር አብይ አህመድ በእውነት ይህን ተረድተው ለግል ቁስ እንደማይጨነቁ፣ ነግረውናል፡፡ ይልቁንም መስጠትን እየሰበኩ፣ አሻራ አኑሩ እያሉን ነው፡፡ ይህን ማመን፣ አምነንም ይህን መስበክ ይኖርብናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይታመኑ ቢቀሩ እዳው ከሳቸው አልፎ ለልጆቻቸው ይተርፋል፡፡ ያመንን እና የተገበርን ደግሞ እናተርፍበታል፡፡ ልጆቻችን ከቁስ አላቀን ከተፈጥሮ ጋር አዋደን ልናሳድግ ይገባል፡፡
 ከተፈጥሮ አና ሀገር በቀል እውቀት ጋር መጣላት
ልንጋፈጣቸው ከሚገቡን መሰረታዊ ችግሮች አንዱ የሆነው ከተፈጥሮ እና አገር በቀል እውቀቶች መጣላታችን፤ በምትኩ በምዕራብ መጤ ሽብርቅርቅ ተጠምደን መባከናቸን ነው፡፡ የተፈጥሮ ፀጋዎችን መተው ብቻ ሳይሆን፤ በዘፈቀደ ማውደም ላይ ተጠምደናል፡፡ ደን ተከላን እንቃወማለን፣ ለመፋቂያ የሚሆን እንጨት ለማግኘት ብዙ ርቀት እንጓዛለን፡፡ መፋቂያ ማዘመን ትተን፣ የጥርስ ቡርሽ ማስታወቂያ ተገዥ ሆነናል፡፡ ለውዝ፣ ኮኮናት፣ ቡና፣ የቅባት እህል፣ ወዘተ ሽጠን ቸኮሌት፣ ካፌን፣ ዘይት፣ ማስቲካ ወዘተ .. ከውጭ እናስገባለን፡፡ ተፈጥሮ የሰጠንን/ኦርጋኒክ የሚባለውን ትተን፣ በኬሚካል የተሰሩ ምርቶች አፍቃሪ ሆነናል፡፡ በከተማችን መናፈሻ አጥፍተን ፎቅ እንገነባለን፡፡ ለዚህ ሁሉ ማድረጊያ የሚስፈልገን ገንዘብ ከውጭ በብድር ጭምር እንወስዳለን፡፡ በመጨረሻ በእዳ ተዘፍቀን በዶላር እጥረት አንማስናለን፡፡
ፈረንጆቹ ከተፈጥሮ ጋር ለመታረቅ ሶፋ ላይ ከመቀመጥ፣ መሬት ላይ መሆን፣ በጫማ ከመሄድ ቢያንስ በቤታችን በእግራችን በመሆን ከተፈጥሮ ጋር መገናኘት (Ground to Earth)፣ አፈርን በእጅ መንካት፣ በአፍንጫ ማሽተት፤ ተክሎችን በጊቢያችን ማሳደግ፤ ጠቃሚ ነው ብለው ይተገብራሉ፡፡ እኛ ቢያንስ መሰረታዊ የመድሃኒትነት ባህሪ ያላቸውን (ዳማከሴ፣ ጤናዳም፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ወዘተ..) በቅጥር ጊቢያችን በቀላሉ ማግኘት፤ የሚያስችል ሁኔታ ውስጥ ሆነን፤ ከኒውክለር ፊዚክስ እኩል እንዴት ከባድ ይሆንብናል? ሚስጥሩ ዘመናዊ የሆንን መስሎን ከተፈጥሮ መጣላት፤ አገር ብቀል እውቀት መናቅ ነው፡፡ መፍትሔው ወደ ቀድሞ ነገራችን ተመልስን በጥሞና መመርመር፤ ራስን ማክበር፣ ከውጭም ቢሆን መርጦ መውስድ ነው፡፡
መፍትሔው ችግኝ በመትከል ስም ዛፍ መተከል አይደለም፡፡ አገር በቀል የሆኑት የብዝሃ ሕይወቶች መርጦ እንዳይጠፉ ብቻ ሳይሆን እንዲበዙ ማድረግና መጠቀም ነው፡፡ የማገዶ ዛፍ ብቻ ሳይሆን የሚያስፈልገን፣ በምግብ እህል እራሳችንን እንድንችል የሚያደርጉ፣ ህፃናትን ከመቀንጨር የሚጠብቁ ብዙ ተክሎችን ከዘመቻ ስሜት ወጥተን መደበኛ ሥራችን ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ጊቢያችንን ሙሉ ሴራሚክስ አድርገን፣ በእግራችን ልንንጎራደድ የምንችልበት ቦታ አይገኝም፡፡
ባለሞያዎች፤ ለሁሉም በሽታ መድሓኒቱ፤ ከውስጥ የሚመነጭ የተፈጥፎ ሀይል ነው ይላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከተፈጥሮ የሚገኝ ነው፡፡ ቻይናዎች ኽርባል ተፈጥሮዋዊ መድሐኒት በሚል ለዓለም እያቀረቡት ይገኛለ፡፡ የዘመናዊ መድሃኒቶች መሰረቱም ይህ የተፈጥሮ ስጦታ ነው፡፡ ተፈጥሮን አፍሪካ ታክብር፣ መሪዎች ይህን ያድርጉ ብለው እየመከሩን ነው፡፡ የችግኝ ተከላው ከተፈጥሮ ጋር የሚያስታርቀን እንዲሆን አስበን እንስራ፡፡
ማዕበራዊ ዕሴት መላሸቅ
ከወንድሜ ጋር በነበረን ውይይት አንዱ ትልቁ ነጥብ አፍሪካዊያን እየተውነው የመጣነው፣ የመወለድ መብት (Birth Right) ጉዳይ ነው፡፡ የመወለድ መብት ቀድሞ በመወለድ ብቻ የሚገኝ መብት ነው፡፡ ታናሽ፤ ታላቁን ማክበር፡፡ ታላቅ ለታናሹ ከለላ መሰጠት፡፡ ይህ በተፈጥሮ በሚገኝ ቀድሞ በመወለድ ብቻ የሚገኝ መብት ነው፡፡ ሌላው ወላጆች ያላቸው ሚና ነው፡፡ ወላጅ ልጅ ጭልጥ ብሎ ሲያንቀላፋ፤ የልጁን ትንፋሽ ማዳመጥ በተፈጥሮ ያለ የፍቅር ስጦታ ነው፡፡ እነዚህ በቤተሰብ የሚጀምሩ የመልካም ማዕበራዊ ግንኙነት መሰረት ናቸው፡፡ ይህን መልካም እሴት፣ በጥሰን ጥለናል፡፡ አሁን የምንፈጥረው ግንኙነት የትኛው ወንድሜ በቁስ የላቀ ነው ወደሚል ተቀይሯል፡፡ ዶላር የሚልክ፤ በውጭ የሚኖር የበለጠ “ክብር” ይሰጠዋል፡፡ ከቤተሰብ የበጠስነው እሴት፤ ታላቅን የማክበር፣ ታናሽን የመንከባከብ፣ ወላጅን መታዘዝ፤ ፤ በማሕበረሰብ ደረጃ ለአረጋዊና ሽማግሌ ክብር፣ በእድሜ ለሚገኝ ፀጋ አውቅና መስጠት ተስኖናል፡፡ ለዚህም ነው በቅርቡ በአርባ ምንጭ አካባቢ እንጥፍጣፊ የሽምግልና በጎ ምግባር ሰናይ፤ ብርቅ ሆኖብን የቦረቅነው፡፡ በቤተሰብ ደረጃ ማዕድ ከበን መቋደሱ፣ በሶፋ ላይ ወይም በቁንን የምግብ ጠረጴዛ ዙሪያ በቁርጥ እንጀራ መቀየሩ፣ በመሶብ ዙሪያ የሚገኘውን የማሕበራዊ እሴት አሳጥቶናል፡፡ ይህን ዕሴት ወደ ቀድሞ ለመመለስ እጅግ ብዙ ስራ ይጠበቅብናል፡፡ በቅድሚያ በቤታችን መከባበር፤ ቀጥሎ ጎረቤት ማክበርና ማገዝ ያስፈልገናል፡፡ ይህ ድምር ለአካባቢ ሰላም ይጠቅመናል፡፡ የጋራ ባለአገርነት ሰሜት ይፈጥርብናል፡፡
እንደ ፈረንጆቹ ዘመናዊ የማሕበራዊ ዋስትና ስርዓት ሳንዘረጋ፤ የራሳችንን በጥሰን፤ አዛውንቶችን፣ ሕፃናትን ለጎዳና ኑሮ የዳረግነው፡፡ ይህን ሊያደርጉ የሚጠበቅባቸው ቤተ እምነቶቻችን፣ የእምነት አባቶች፣ ለዚህ በጎ ምግባር ሊያሰልፉን አልቻሉም፡፡ ከእብደታችን ተገሳፅ ሰጥተው ተዉ የሚሉ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ይልቁንም እንደ ዓለማዊያን ሁሉ እነርሱም በመንግሥት እግር ሥር ወድቀው ልማታዊ ሆነው፤ ክብርም ሞገስም አጥተዋል፡፡ በቅርቡ በእምነት ተቋማት ቀድመው በውስጣቸው ያለውን ሰንኮፍ ነቅለው፤ ቶሎ ወደ ምህመኑ ይመጣሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ የዛኔ ለማህበራዊ ስብራታችን ጠጠር ያስቀምጣሉ፡፡

Friday, April 26, 2013

የፕሮፌሰር በየነ የዲሞክራሲ አርበኝነት ሸፋፋ ሚዛን ይብቃው ብንልስ?



girmaseifu32@yahoo.com
ይህን ፅሁፍ ስፅፍ ሰሜቴን ለመቆጣጠር እየሞከርኩ ብቻ ሳይሆን መቆጣጠሬንም እርግጣኛ መሆን ፈልጌ ነው፡፡ ባይሆን ኖሮ እኛ ሰፈር እንደሚባለው አንቱ ብሎ ስድብ ሰለማይኖር መልሴን መፃፍ የፈለኩት የነበረው ፕሮፌሰር የሚለውን ማዕረግ ባለመጠቀም ነበር፡፡ ምክንያቱም በተደጋጋሚ አንድ ፀጉረ ልውጥ ፣ አንድ መርካቶ  አካባቢ የተወዳደረ ሰው፣ ወዘተ እያሉ ሰሜን ለመጥራት እና አሰተያየት ለመስጠት እንዴት እንደሚጠየፉት ስለገባኝ ነው፡፡ በዚህ ልክ መውረድ ሰለአልፈለኩ በክብር መልስ መስጠት ወስኛለሁ፡፡ ማለትም ስሜቴ በቁጥጥር ስር ውሎዋል ማለት ነው፡፡
ለፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እኔን አሰመልክተው ስለሚሰጡት አሰተያየት መልስ መስጠት ከነበረብኝ ረጅም ጊዜ አልፎታል፡፡ ምክንያቱም እኔና ፕሮፌስር በየነን በምንም የስራ አጋጣሚ ተገናኝተን ሰለማናውቅና በምርጫ 2002 ምርጫ በነበሩበት ሰሜት አንፃር ሆኖ ሲታይ መገመት መብት ባይሆንም ልምድ ሰለሆነ ሰዎች ሰለማያውቁት ነገር ሲገምቱ ሰህተት ሊሰሩ ይችላሉ በሚል ቅን አሰተሳሰብ ችላ ብዬ አልፌዋለሁ፡፡ እርሳቸውን ያኮረፏቸው የፓርቲ ሰዎች እኔንም እየመከሩኝ፡፡ ነገር ግን ከሁለት አመት ከሰድስት ወር በላይ እየገመቱ መሳሳት በእርሳቸው ደረጃ ላለ ሰው ተገቢ ነው ብዬ መውስድ ስለአልፈለኩ ምክርም አልሰማም ሰለአሉ መልስ በአደባባይ በሚመጥናቸው ልክ መስጠት ተገቢ ነው ብዬ ወስጄዋለሁ፡፡
ፕሮፌሰር በየነ በቅርቡ በአዲስ ጉዳይ መፅሔት በሰጡት አሰተያየት “በጣም የሚገርመው በ2002 ምርጫ አንድ ግለሰብ ከመድረክ ውስጥ በተአምር አሸንፏል እንዳለ እሰከዛሬ የማይገባኝ ነው፡፡” ብለዋል፡፡ እንደተማረ ሰው እንዲገባዎ ከፈለጉ የተመረጠውን ሰው መጠየቅ ነው የሚጠቅመው? ወይስ ግራ እንደተጋቡ ይህን ያህል ጊዜ መቆየት ነው? ይህ ጥፋት የማን ሊሆን ይችላል? በዚህ ደረጃ ለሚገኝ ሰው ይህን ያህል ግድየለሽ (Ignorant) መሆን ይቻላል? በእኔ ግምት የሚቻል አይመስለኝም፡፡
ፕሮፌሰር በየነ በዚሁ መፅሔት በሰጡት አሰተያየት “ስንትና ስንት የዲሞክራሲ አርበኛ ባሉበትና ስንት ጊዜ ደጋግመው ያሸነፉ ህዝብ የሚያውቃቸው እያሉ ሁሉንም ተሸንፈዋል ብለው አንድ ከመርካቶ አካባቢ የተወዳደረ ሰው አሸንፏዋል ብሎ ማወጅ ያሳፍራል፡፡” ብለዋል:: ስንት ቢሆን ነበር የማያፍሩት፣ እርሶ ቀድሞ በተደረጉ ምርጫዎች ደግመው ሰለተመረጡ አርበኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጠ ባንዳ (በኢህአዴግ የተገዛ) ማለት እራሳዎን አርበኛ ለማድረግ የተጠቀሙበት የአርበኝነት ሚዛን ሸፋፋነት ነው የሚያሳየው፡፡ ፕሮፌሰር በየነ የኢትዮጵያን የምርጫ ስርዓት በደንብ የሚያውቁት ይመስለኛል ተቆጥሮ ውጤት ሳያልቅ እንዴት አንድ ሶስተኛ ውጤት መድረክ እንዳገኘ አወቁት፡፡ ይህንንም በረከት ይሆና የነገራቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከሶሰት መቶ ሰማኒያ ሺ ህዝብ በላይ ለመድረክ ድምጽ የሰጠ ሲሆን ያገኘው ግን አንድ መቀመጫ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሌላ አማራጭ የምርጫ ስርዓት የምንከተል ቢሆን ኖሮ ቢያንስ እርሳቸው እንደሚሉት አንድ ሶስተኛ ልናገኝ እንችል ነበር፡፡ በሌለ ስርዓት ግን የፓርላማ ወንበር በአርበኝነት (ባለፈው ተመርጫለሁ በሚል) መጠየቅ አይቻልም፡፡
ፕሮፌሰር በየነ በመቀጠልም እኔ ወደ ፓርላማ የገባሁበትን መንገድ እርሳቸው አላውቅም ብለው አላቆሙም ግርማ ፓርላማ እንዴት እንደገባ መልሱን የሚያውቀው ኢህአዴግ ነው ብለዋል፡፡ እንዲህም ብለው ይቀጥላሉ “የቀረው ሁሉ ወድቆ አንድ ብቻ ተወካይ አልፏል መባሉ አሳማኝ አይደለም፡፡” በ1997 ምርጫ ቅንጅት አዲስ አበባን በሙሉ ወንበር አሽንፎ አንድ ተመራጭ ብቻ ከኢህአዴግ ተመርጦ ነበር፡፡ ይህ ምርጫም ተቀባይነት የለውም ነው የሚሉት፡፡ ከዚህ በፊት በፓርላማ ሻለቃ አድማሴ የሚባሉ ሰው ብቸኛ የፓርላማ አባል ነበሩ፡፡ እና እርሳቸውንም ያስመረጣቸው የኢህአዴግ ድራማ ነው ብለው ይወስዱታል፡፡ አላውቅም ማለት ጨዋነት ነው የማያውቁትን ለመጠንቆል መፈለግ ግን ከእርሶ አይጠበቅም፡፡ ቢያንስ ማዕረግ ባገኙበት ሳይንስ ዘርፍ አሰቸጋሪ የሚባሉ መረጃዎች እንዴት እንደሚገኝ የሚረዳ ስልት ያውቃሉ ብዬ ስለማምን፡፡
ለነገሩ ፕሮፌስር በየነ የተፈጥሮ ሳያንስ ያልሆነው ዘርፍ የሚሰጠውን ድምዳሜ መድረሻ ዘዴ (በተፈጥሮ ሳይንስ አንድ እና አንድ ሁለት፣ ሁለት እጅ ሃይድሮጅን እና ኦክስጅን ውሃ፣ ወዘተ ሰለሆነ ማንም የተለየ መደምደሚያ መድረስ አይችልም) ክፍተት ተጠቅመው ችግር በገጠማቸው ቁጥር ማሳበቢያ የሚያደርጉት ኢህአዴግ ነው፡፡ ኢህአዴግ እጁ ረጅም ብቻ ሳይሆን ሰለታም መሆኑ ቢታወቅም ለሁሉም ችግራችን ማሳበቢያ ማድረግ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ በአንድ ወቅት አብረን በተገኘንበት ስብሰባ በፓርቲያቸው ውስጥ ወጣቶችን ለምን ወደፊት አታመጡም ሲባሉ የኢህአዴግ ወሬ ነው ብለው ሲመልሱ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ የኢህአዴግ ወሬ ከሆነ ለምን አንድነት ወጣቶችን ወደፊት ያመጣል? ተብለው እንደሚጠየቁ የሚያስቡ አይመስለኝም፡፡ ለፕሮፌስር በየነ ጥያቄ ሁሉ ከባድ ሲሆን ወይም የግል ግዴለሽነታቸው ሲያመዝን የኢህአዴግ ድራማ ነው ማለት ቀላል መውጫ አድርገውታል፡፡
ይህን ፅሁፍ ለእትመት የበቃ ዕለት እኔ እና እርሶ አብረን ነበርን ስብሰባ ላይ፡፡ ምን አልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ ፈገግ ብለው ሰላምታ የሰጡኝ የዛን ዕለት ነው፡፡ በዚያን ዕለት በስብሰባ ላይ ለተነሳ አስተያየት መልስ ሲሰጡ ለሌለ ጊዜም የህይወት መርዕ ቢሆን ጥሩ ነው ያሉዋትን ወድጄሎታለሁ፡፡ መረጃ ሳይኖር ያለመናገር የምትለው ነች፡፡ ልክ ነው፡፡ ይህ መርዕ ግን ለእርሶም የሚሰራ መሆን አለበት መረጃ በሌሎት ጉዳይ 30 ወር ሙሉ መገመት ከዚያም መሰለኝ  እና ደስአለኝ ብሎ አሰተያየት መስጠት አይገባም፡፡ እርሶን የሚያክል የፖለቲካ ሰብዕና ያለው ሰው ከተራ ግምት ለመውጣት በማሰብ እና ከአኔ ሌላ ላሳር ብለው ከሚታበዩ ለምንድነው አንድ ቀን እንኳን ያለቦትን የመረጃ ክፍተት ለመድፈን ከእኔ ጋር መረጃ መለዋወጥን እንደ ነውር ቆጥረው በየሚዲያው ላይ እንደፈለጉ በግል ተገቢ ያልሆነ አሰተያየት የሚሰነዝሩት፡፡ በነገራችን ላይ በ1997 ምርጫ በተነሳው ጉዳይ መረጃ የላችሁም ያሉበት እንደምታ ሌላ ቦታ የሚነሳ ቢሆንም በ1997 ማን? የት? እንደነበር ይታወቃል፡፡ እርሶ ስለአላወቁት ግን የለም ብለው ያለመረጃ መናገር ጥሩ አይደለም ያሉትን የህይወት ምርዕ መጣስ ቢያቆሙ ጥሩ ነው፡፡
ፕሮፌሰሩን መፅሔቱ ጠንከር አድርጎ እውነት እንዲናገሩ ሲገፋቸው፣ ኢህአዴግ ፈልጎት ነው ያሰቀመጠው ነው የሚሉት? ለሚለው ጥያቄ የሰጡት መልስ፡፡ “ይህ አባባሌ አልተወደደልኝም፡፡ ግን የኢህአዴግ ድራማ አካል ሊሆን ይችላል፡፡” ብለው መልሰዋል፡፡ የምን ፈራ ተባ ነው አዎ ብሎ የሚከተለውን ጥያቄ መመለስ አይሻልም፡፡ ለምን ብሎ? ከዚያስ ምን እያደረገ ነው ለኢህአዴግ? ወዘተ. ስለ እርሶዎ  ሁለት ዙር ፓርላማ ሰለመመረጦ ማስረጃ ያቀረቡት ግን አስቂኝ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ምስክርነት ስጥቶ ነው ይሉናል፡፡ ለእርሶ ጊዜ የምርጫ ቦርድ ምስክርነት ትክክል እና በቂ ይሆናል፡፡ ለኔ ምርጫ ቦርድ ምስክርነት አልሰጠውም ብለው ገምተው ለመሳሳት ወስነው መሆን አለበት፡፡ የሚገርሞት ለኔ ምርጫ ቦርድ ሳይመሰክር በፊት እያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ የተገኘውን ውጤት ልክ ምርጫ ሲጠናቀቅ ይዤ ነበር፡፡ ይህንኑ ነው ያረጋገጠው፡፡ ለእርሶ ግን መሸነፎን ሁሉ የነገሮት ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ምክንያቱም በምርጫ ጣቢያ አልነበሩማ፡፡ በግድ መኖር ባይጠበቅቦትም ይህን ሊያድርግ የሚችል ሁነኛ አካል አልፈጠሩም፡፡ ግምት አይደለም፡፡ እስኪ መረጃ ካሎት በየምርጫ ጣቢያ ያገኙትን ውጤት ለህዝብ ይፋ ያድርጉ፡፡
ክቡር ፕሮፌስር ሰለ ምርጫ ውጤት ጉዳይ ያለኝን አቋም ልንገሮት ኢህአዴግ ምርጫውን ከቻለ በትክክል ለማሸነፍ ካልቻለ ደግሞ በየምርጫ ጣቢያ ባሰማራቸው ታዛቢና አሰመራጮች አማካይኝነት የምርጫ ውጤቱን ማስለወጥ የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ እንደተዘጋጅ አውቃለው፡፡ ለዚህም ህገወጥ የሆኑቱን ተገባራት ሁሉ ከማድረግ እንደማይመለስ አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ በፍቼ ለታዛቢነት የላክናቸውን ልጆች ያደረጉትን፤ በትግራይ በአቶ ስዬ ምርጫ ጣቢያ ያሳየውን ባሕሪ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በከተማ ደግሞ የተለየ ነበር፡፡ በከተማ የተዘጋጀውን ከመከላከል አንፃር እኔ ምርጫ ክልል መቶ በመቶ በቁጥጥራችን ስር አድርገን ተወዳድረናል፡፡ በውጤት ካልተለካ በስተቀር መቶ በመቶ አልተሳካልንም፡፡ ዝርዝሩን ሌላ ጊዜ በሌላ መልክ እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡ ጠቃሚ ነው ብዬ ስለማምን፡፡ እርሶ ግን ያልተመረጡት ምርጫውን በማንኛውም መንገድ ለማሸነፍ ከቆረጠው ኢህአዴግ ጋር የሚመጥን ዝግጅት በምርጫ ክልል ስለአላደረጉ ነው የተሸነፉት፡፡ ይህንን ለማስረዳት በተወዳደሩበት ምርጫ ክልል ሰንት ታዛቢ አሰማርተዋል? ሰንቶቹ ታዛቢዎች ኢህአዴግ አሰፈራራን ብለው ጥለው ወጡ? በተወዳደሩበት ምርጫ ጣቢያ የተገኘውን ውጤት በሙሉ ቆጥረው ተቀብለዋል? በውድድሩ ወቅት ለምርጫው የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟልተው ነው የተወደሩት? (ወደ ዝርዝር አልገባም እንዳላደረጉት ሰለማውቅ)፡፡ በረከት ታሸንፋለህ ብሎኛል ብለው ምርጫ ጣቢያዎን ለዕድል ጥለው አዘርፈው አንድም ቢሆን ያሸነፈን ሰው ኢህአዴግ ነው የሰጠው ብሎ እኝኝ ማለት ምን ይባላል፡፡ ለኢህአዴግ ከኔ ይልቅ በምንም መስፈርት እርሶ እንደሚቀርቡት ማንም ያውቃል፡፡ ኢህአዴግ በሰራው ድራማ ተመርጨ ብሆን አንኳን ባለፈው ፓርላማ ዘመን ምን ምን ለኢህአዴግ እንደሰራው ማስረጃ አቅርበው አይሞግቱኝም?
የእኔን ለኢህአዴግ ቅርብ መሆን እና አለመሆን ማወቅ ከፈለጉ አልፎ አልፎ የማውጣቸውን ሁለገብ ፅሁፎች ማንበብ ነው፡፡ እነዚህ ፅሁፎች የሚቃኙበትን አሰተሳሰብ ሊረዱት ይችላሉ፡፡ የሚገርሞት ይህ አስተሳሰቤ ደግሞ ኢህአዴግ መሆንንም አጥያት አያደርገውም፡፡ ለዚህም እኮ ነው በአሰተሳሰብ እርሶ ለኢህአደግ  እንደሚቀርቡ ብናውቅም ትግሉ አሁን የርዕዮታ ዓለም ፍልስፍና ጉዳይ ሳይሆን መሰረታዊ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጉደይ ሰለሆነ ነው በመድረክ አብረን የምንሰራው፡፡ ይህ ደግሞ ሰው መሆን ብቻ በቂ ስለሆነ ነው፡፡ ነውርነት የለውም፡፡ በሀገራችን ምቹ ምዕዳር ተፈጥሮ የፖለቲካ ጫወታው የርዕዮት ዓለም ጉዳይ በሚሆንበት ወቅት፤ ለኢህአዴግ ቅርብ የሚሆኑት እርሶ ሰለሚሆኑ ኢህአዴግ በካድሬነት ባይችሉ እንኳን ለአማካሪነት የሚፈልጎት እርሶ እንደሚሆኑ አንድም ጥርጥር አይኖረኝም፡፡ ዕድሜና ጤና ከተገኘ፡፡ በኢህአዴግ መንግሰት ሚኒስትር የሆኑትና ለኢህአዴግ ፕሬዝዳንት ለመሆን የተወዳደሩት እርሶ መሆንዎን መዘንጋት የለቦትም፡፡ ቅርብ መሆንዎን ለማሳየት ብቻ ነው ይህን ያነሳሁት፡፡ እኔ ግን የኢህአዴግን ስልጣን ወድቆ ባገኝ እንዲያነሱት ከመንገር ውጭ ልመኘውና ልወስደው አልችልም፡፡ እኔና ኢህአዴግ የሚያገናኘን ሀገር እንጂ ርዕዮታለማዊ መስመር የለንም፡፡ ግልፅ ነው ብዬ ልውሰደው?
ግርማ ሠይፉ ማሩ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ከቁራና ከዳዊት የቱን ይመርጣሉ? ከተከበሩ ግርማ ሠይፉ ማሩ



አልፎ አልፎ ጠዋት የማገኛቸው የማኪያቶ ቡድን አለ፡፡ በፓርላማ ሰለነበረው ውሎ መሠረት አድርገው የግል አሰተያየት ይሰጣሉ በዚህ መሃል አንዱ ምሳሌያዊ ንግግር አደረገ ወደድኩትና ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡ ቁራ ታውቃላችሁ በተለይ መሬት ላይ በእግሯ ስትሄድ አታምርም ይህ ችግር እንዳለባት ታውቃለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእርግብ አካሄድ ይማለርካታል፡፡ አካሄዷን ለማሳመር እንደ እርግብ መሄድ ይኖርብኛል ብላ ወሰነችና ልምምድ ጀመረች፡፡ አስር ዓመት ሙሉ ቤት ዘግታ ስትለማመድ ቆይታ ሳይሳካላት ይቀርና ተስፋ በመቁረጥ አንድ ውሣኔ ላይ ትደርሳለች ቢያስጠላም በራሷ በቀድሞ አካሄድ እንደ ቁራ ለመሄድት ወስናለች፡፡የሚያሳዝነው ነገር ግን የእርግብንም ሳትለምድ የራሷም የቁራ አካሄድ ጠፋባት፡፡
የዚህ ምሳሌ መነሻ የሆኑት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ናቸው፡፡ በምክር ቤት ውስጥ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ለመምሰል ሲያደርጉ የነበረውን ሙከራ የትዝብቱ አንድ አካል ነው፡፡ በዚህ ዕይታ ሙሉ በሙሉ ባልስማማም ፍፁም ውሽት ነው ራሳቸውን ነበር የነበሩት ብዬ ልከራከር አልችልም፡፡ እኔም የሆነ ነገር ታይቶኛል፡፡ ስለዚህ ይህ ማሳሰቢያው አቶ ሀይለማሪያም መለስን ላይሆኑ ሀይለማሪያምን እንዳያጡት የተሰጠ ምክር በመሆኑ በበጎ ወስጀዋለሁ፡፡
የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ በደንብ በሚያውቁት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ላስረዳ፡፡ መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ምዕራፍ 17 ዝርዝሩን ማየት ይቻላል በአጭሩ ታሪኩ የጎሊያድና የዳዊት ነው፡፡ ንጉስ ሳኦል ዳዊት ጎልያድን ለመግጠም ይመረጥና ይልከዋል ወደ ፍልሚያው ሊገባ ሲል፤ ሳኦል ለዳዊት እንዲጠቅመው በሚል የንጉሱን ካባና ንጉሱ በጦርነት ጊዜ የሚጠቀምበትን ዋነኛ መዋጊያ የሆነ የናስ ቁር ደፋለት፤ ጥሩርም አለበ ሰው፡፡ የንጉሱን ልብስ ለብሶ መንገድ ሲጀምር አልተመቸውም አውልቁልኝ ብሎ አወለቀው፤ በማስከተልም የተሰጠውን ትጥቅ ይቅርብኝ ብሎ ወንጭፌን አምጡ አለ፡፡ ከዚያም ብዙዎቹ በዚህ አለባበስና በወንጭፍ እንዴት ጎልያድን የሚያክል ግዙፍ ሰው ለማሸነፍ እንደሚችል ሲጠየቅ ጎልያድ እንደምታዩት ትልቅ ነው (የጎልያድ ቁመት ከስድስት ክንድ በላይ ነው) ለኔ ጎልያድን መምታት ሳይሆን መሳት ነው ከባድ ይላቸዋል፡፡ ግጥሚያው ሲጀመርም ዳዊት ጎልያድን በወንጭፍ ግንባሩን ብሎ ጣለው፡፡ እንዳለውም ጎልያድን መምታት ሳይሆን ከባድ መሳት ከባድ መሆኑን አስመሰከረ፡፡ ዳዊት ያደረገው ከንጉሱ ካባ ይልቅ የራሱ ደበሎ፤ ከንጉሱ ዘመናዊ መሳሪያ ይልቅ የራሱ የሚያውቀው ወንጭፍ እንደሚሻል አሰመሰከረ፡፡ እዚህ ጋ ለአቶ ሀይለማሪያም የተላለፈው መልዕክት የንጉሱ ሌጋሲ ማስጠበቅ በሚል ሳይሆን በራሳቸው ደበሎና ወንጭፍ እንዲጠቀሙ ለማሳሰብ ነው፡፡
እነዚህ ሁለት ምሳሌዎች ለአቶ ሀይለማሪያም በጣም ጥሩምሳሌዎች ናቸው፡፡ ምርጫው እንደ ቁራዋ ሌላ ለመሆን ሞክሮ እራሳቸውንም መሆን አቅቶዋቸው ሳይሳከላቸው መቅረት ወይም እንደ ዳዊት የንጉሱን ትተው እራሳቸውን መሆን ነው፡፡ ምርጫው የግል ነው የኛ ጉዳይ መምከር ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሳቸውን እንዲሆኑ የምፈልግበት አንድ ሁለት ነጥብ ላንሳላችሁ አንድ የፕሬስ ህግ የመናገርና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የንግድ ህግ መሆኑን አናውቅም ነበር፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች በንግድ ህግ ብቻ የሚጠቀሱ ቢሆን ኖሮ በፍትሕ ብሔር ህግ እንጂ በህገመንግስት ውስጥ የሚጠቀሱ አይሆኑም ነበር፡፡ የህገ መንግሰቱን አንቀፅ 29/2 እና ሌሎችም ድንጋጌዎች እንዳይሸራረፉ መጠየቅ በንግድ ህግ እንዲታይ ማለት ተገቢ አይደለም፡፡
ነጋዴዎች የያዙትን የንግድ ቤት በሽያጭ ይተላለፍ የሚል አስተያየት ሲሰጥ ይህ ዓላማው ድሃው እንዲኖርበት ነው ማለት የእውቀት ሳይሆን ጉዳዩ ሌላ ነው ፣ ድሃው የሚኖርበት ቤትም ቢሆን ለድሃ በይዞታነት ይተላለፍ ማለት ይቻላል፡፡ በጥያቄ የቀረበላቸው ግን ነጋዴዎች እየነገዱ ያሉበትን ቤት ባለቤትነት አዛውሩና ገንዘብ ተቀበሉ፡፡ የተቀበላችሁን ገንዘብ ደግሞ ለኢንቨስትመንት አውሉት ማለት ለወዳጅ የተሰጠ ምክር ነው፡፡ ልብ ብለው ያድምጡኝ ይህ ምክር ከተቀናቃኝም ቢሆን ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ ለነገሩ ዓላማው እራሱን ችሎ የሚኖር ነጋዴንም ቢሆን በጭሰኝነት መያዝ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ ለነፃነት ስንል ጫካ ገባን የሚል ቡድን የዜጎቸን ነፃነትን ለመገደብ ምንም መንገድ እንደሚጠቀም ማሳያነው፡፡ ይህ ደግሞ ጫካ የመግባታቸው ሚስጥር ለነፃነት ነበር የሚለው ነጭ ውሽት እንደሆነ መረዳት ከበድ አይሆንም፡፡ ነፃነትን የሚያከብር ቡድን በምንም ዓይነት የሌሎችን ነፃነት በቁሳዊ ጉደይ ለመያዝ አይጥርም፡፡ ነፃነት የማያውቅ ነፃ አውጭ የሚለው የሚገልፃችሁ ይመስለኛል፡፡

Girma Seifu Minneapolis Flyer


Girma Seifu Picture 2