Friday, April 26, 2013

የፕሮፌሰር በየነ የዲሞክራሲ አርበኝነት ሸፋፋ ሚዛን ይብቃው ብንልስ?



girmaseifu32@yahoo.com
ይህን ፅሁፍ ስፅፍ ሰሜቴን ለመቆጣጠር እየሞከርኩ ብቻ ሳይሆን መቆጣጠሬንም እርግጣኛ መሆን ፈልጌ ነው፡፡ ባይሆን ኖሮ እኛ ሰፈር እንደሚባለው አንቱ ብሎ ስድብ ሰለማይኖር መልሴን መፃፍ የፈለኩት የነበረው ፕሮፌሰር የሚለውን ማዕረግ ባለመጠቀም ነበር፡፡ ምክንያቱም በተደጋጋሚ አንድ ፀጉረ ልውጥ ፣ አንድ መርካቶ  አካባቢ የተወዳደረ ሰው፣ ወዘተ እያሉ ሰሜን ለመጥራት እና አሰተያየት ለመስጠት እንዴት እንደሚጠየፉት ስለገባኝ ነው፡፡ በዚህ ልክ መውረድ ሰለአልፈለኩ በክብር መልስ መስጠት ወስኛለሁ፡፡ ማለትም ስሜቴ በቁጥጥር ስር ውሎዋል ማለት ነው፡፡
ለፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እኔን አሰመልክተው ስለሚሰጡት አሰተያየት መልስ መስጠት ከነበረብኝ ረጅም ጊዜ አልፎታል፡፡ ምክንያቱም እኔና ፕሮፌስር በየነን በምንም የስራ አጋጣሚ ተገናኝተን ሰለማናውቅና በምርጫ 2002 ምርጫ በነበሩበት ሰሜት አንፃር ሆኖ ሲታይ መገመት መብት ባይሆንም ልምድ ሰለሆነ ሰዎች ሰለማያውቁት ነገር ሲገምቱ ሰህተት ሊሰሩ ይችላሉ በሚል ቅን አሰተሳሰብ ችላ ብዬ አልፌዋለሁ፡፡ እርሳቸውን ያኮረፏቸው የፓርቲ ሰዎች እኔንም እየመከሩኝ፡፡ ነገር ግን ከሁለት አመት ከሰድስት ወር በላይ እየገመቱ መሳሳት በእርሳቸው ደረጃ ላለ ሰው ተገቢ ነው ብዬ መውስድ ስለአልፈለኩ ምክርም አልሰማም ሰለአሉ መልስ በአደባባይ በሚመጥናቸው ልክ መስጠት ተገቢ ነው ብዬ ወስጄዋለሁ፡፡
ፕሮፌሰር በየነ በቅርቡ በአዲስ ጉዳይ መፅሔት በሰጡት አሰተያየት “በጣም የሚገርመው በ2002 ምርጫ አንድ ግለሰብ ከመድረክ ውስጥ በተአምር አሸንፏል እንዳለ እሰከዛሬ የማይገባኝ ነው፡፡” ብለዋል፡፡ እንደተማረ ሰው እንዲገባዎ ከፈለጉ የተመረጠውን ሰው መጠየቅ ነው የሚጠቅመው? ወይስ ግራ እንደተጋቡ ይህን ያህል ጊዜ መቆየት ነው? ይህ ጥፋት የማን ሊሆን ይችላል? በዚህ ደረጃ ለሚገኝ ሰው ይህን ያህል ግድየለሽ (Ignorant) መሆን ይቻላል? በእኔ ግምት የሚቻል አይመስለኝም፡፡
ፕሮፌሰር በየነ በዚሁ መፅሔት በሰጡት አሰተያየት “ስንትና ስንት የዲሞክራሲ አርበኛ ባሉበትና ስንት ጊዜ ደጋግመው ያሸነፉ ህዝብ የሚያውቃቸው እያሉ ሁሉንም ተሸንፈዋል ብለው አንድ ከመርካቶ አካባቢ የተወዳደረ ሰው አሸንፏዋል ብሎ ማወጅ ያሳፍራል፡፡” ብለዋል:: ስንት ቢሆን ነበር የማያፍሩት፣ እርሶ ቀድሞ በተደረጉ ምርጫዎች ደግመው ሰለተመረጡ አርበኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጠ ባንዳ (በኢህአዴግ የተገዛ) ማለት እራሳዎን አርበኛ ለማድረግ የተጠቀሙበት የአርበኝነት ሚዛን ሸፋፋነት ነው የሚያሳየው፡፡ ፕሮፌሰር በየነ የኢትዮጵያን የምርጫ ስርዓት በደንብ የሚያውቁት ይመስለኛል ተቆጥሮ ውጤት ሳያልቅ እንዴት አንድ ሶስተኛ ውጤት መድረክ እንዳገኘ አወቁት፡፡ ይህንንም በረከት ይሆና የነገራቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከሶሰት መቶ ሰማኒያ ሺ ህዝብ በላይ ለመድረክ ድምጽ የሰጠ ሲሆን ያገኘው ግን አንድ መቀመጫ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሌላ አማራጭ የምርጫ ስርዓት የምንከተል ቢሆን ኖሮ ቢያንስ እርሳቸው እንደሚሉት አንድ ሶስተኛ ልናገኝ እንችል ነበር፡፡ በሌለ ስርዓት ግን የፓርላማ ወንበር በአርበኝነት (ባለፈው ተመርጫለሁ በሚል) መጠየቅ አይቻልም፡፡
ፕሮፌሰር በየነ በመቀጠልም እኔ ወደ ፓርላማ የገባሁበትን መንገድ እርሳቸው አላውቅም ብለው አላቆሙም ግርማ ፓርላማ እንዴት እንደገባ መልሱን የሚያውቀው ኢህአዴግ ነው ብለዋል፡፡ እንዲህም ብለው ይቀጥላሉ “የቀረው ሁሉ ወድቆ አንድ ብቻ ተወካይ አልፏል መባሉ አሳማኝ አይደለም፡፡” በ1997 ምርጫ ቅንጅት አዲስ አበባን በሙሉ ወንበር አሽንፎ አንድ ተመራጭ ብቻ ከኢህአዴግ ተመርጦ ነበር፡፡ ይህ ምርጫም ተቀባይነት የለውም ነው የሚሉት፡፡ ከዚህ በፊት በፓርላማ ሻለቃ አድማሴ የሚባሉ ሰው ብቸኛ የፓርላማ አባል ነበሩ፡፡ እና እርሳቸውንም ያስመረጣቸው የኢህአዴግ ድራማ ነው ብለው ይወስዱታል፡፡ አላውቅም ማለት ጨዋነት ነው የማያውቁትን ለመጠንቆል መፈለግ ግን ከእርሶ አይጠበቅም፡፡ ቢያንስ ማዕረግ ባገኙበት ሳይንስ ዘርፍ አሰቸጋሪ የሚባሉ መረጃዎች እንዴት እንደሚገኝ የሚረዳ ስልት ያውቃሉ ብዬ ስለማምን፡፡
ለነገሩ ፕሮፌስር በየነ የተፈጥሮ ሳያንስ ያልሆነው ዘርፍ የሚሰጠውን ድምዳሜ መድረሻ ዘዴ (በተፈጥሮ ሳይንስ አንድ እና አንድ ሁለት፣ ሁለት እጅ ሃይድሮጅን እና ኦክስጅን ውሃ፣ ወዘተ ሰለሆነ ማንም የተለየ መደምደሚያ መድረስ አይችልም) ክፍተት ተጠቅመው ችግር በገጠማቸው ቁጥር ማሳበቢያ የሚያደርጉት ኢህአዴግ ነው፡፡ ኢህአዴግ እጁ ረጅም ብቻ ሳይሆን ሰለታም መሆኑ ቢታወቅም ለሁሉም ችግራችን ማሳበቢያ ማድረግ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ በአንድ ወቅት አብረን በተገኘንበት ስብሰባ በፓርቲያቸው ውስጥ ወጣቶችን ለምን ወደፊት አታመጡም ሲባሉ የኢህአዴግ ወሬ ነው ብለው ሲመልሱ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ የኢህአዴግ ወሬ ከሆነ ለምን አንድነት ወጣቶችን ወደፊት ያመጣል? ተብለው እንደሚጠየቁ የሚያስቡ አይመስለኝም፡፡ ለፕሮፌስር በየነ ጥያቄ ሁሉ ከባድ ሲሆን ወይም የግል ግዴለሽነታቸው ሲያመዝን የኢህአዴግ ድራማ ነው ማለት ቀላል መውጫ አድርገውታል፡፡
ይህን ፅሁፍ ለእትመት የበቃ ዕለት እኔ እና እርሶ አብረን ነበርን ስብሰባ ላይ፡፡ ምን አልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ ፈገግ ብለው ሰላምታ የሰጡኝ የዛን ዕለት ነው፡፡ በዚያን ዕለት በስብሰባ ላይ ለተነሳ አስተያየት መልስ ሲሰጡ ለሌለ ጊዜም የህይወት መርዕ ቢሆን ጥሩ ነው ያሉዋትን ወድጄሎታለሁ፡፡ መረጃ ሳይኖር ያለመናገር የምትለው ነች፡፡ ልክ ነው፡፡ ይህ መርዕ ግን ለእርሶም የሚሰራ መሆን አለበት መረጃ በሌሎት ጉዳይ 30 ወር ሙሉ መገመት ከዚያም መሰለኝ  እና ደስአለኝ ብሎ አሰተያየት መስጠት አይገባም፡፡ እርሶን የሚያክል የፖለቲካ ሰብዕና ያለው ሰው ከተራ ግምት ለመውጣት በማሰብ እና ከአኔ ሌላ ላሳር ብለው ከሚታበዩ ለምንድነው አንድ ቀን እንኳን ያለቦትን የመረጃ ክፍተት ለመድፈን ከእኔ ጋር መረጃ መለዋወጥን እንደ ነውር ቆጥረው በየሚዲያው ላይ እንደፈለጉ በግል ተገቢ ያልሆነ አሰተያየት የሚሰነዝሩት፡፡ በነገራችን ላይ በ1997 ምርጫ በተነሳው ጉዳይ መረጃ የላችሁም ያሉበት እንደምታ ሌላ ቦታ የሚነሳ ቢሆንም በ1997 ማን? የት? እንደነበር ይታወቃል፡፡ እርሶ ስለአላወቁት ግን የለም ብለው ያለመረጃ መናገር ጥሩ አይደለም ያሉትን የህይወት ምርዕ መጣስ ቢያቆሙ ጥሩ ነው፡፡
ፕሮፌሰሩን መፅሔቱ ጠንከር አድርጎ እውነት እንዲናገሩ ሲገፋቸው፣ ኢህአዴግ ፈልጎት ነው ያሰቀመጠው ነው የሚሉት? ለሚለው ጥያቄ የሰጡት መልስ፡፡ “ይህ አባባሌ አልተወደደልኝም፡፡ ግን የኢህአዴግ ድራማ አካል ሊሆን ይችላል፡፡” ብለው መልሰዋል፡፡ የምን ፈራ ተባ ነው አዎ ብሎ የሚከተለውን ጥያቄ መመለስ አይሻልም፡፡ ለምን ብሎ? ከዚያስ ምን እያደረገ ነው ለኢህአዴግ? ወዘተ. ስለ እርሶዎ  ሁለት ዙር ፓርላማ ሰለመመረጦ ማስረጃ ያቀረቡት ግን አስቂኝ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ምስክርነት ስጥቶ ነው ይሉናል፡፡ ለእርሶ ጊዜ የምርጫ ቦርድ ምስክርነት ትክክል እና በቂ ይሆናል፡፡ ለኔ ምርጫ ቦርድ ምስክርነት አልሰጠውም ብለው ገምተው ለመሳሳት ወስነው መሆን አለበት፡፡ የሚገርሞት ለኔ ምርጫ ቦርድ ሳይመሰክር በፊት እያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ የተገኘውን ውጤት ልክ ምርጫ ሲጠናቀቅ ይዤ ነበር፡፡ ይህንኑ ነው ያረጋገጠው፡፡ ለእርሶ ግን መሸነፎን ሁሉ የነገሮት ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ምክንያቱም በምርጫ ጣቢያ አልነበሩማ፡፡ በግድ መኖር ባይጠበቅቦትም ይህን ሊያድርግ የሚችል ሁነኛ አካል አልፈጠሩም፡፡ ግምት አይደለም፡፡ እስኪ መረጃ ካሎት በየምርጫ ጣቢያ ያገኙትን ውጤት ለህዝብ ይፋ ያድርጉ፡፡
ክቡር ፕሮፌስር ሰለ ምርጫ ውጤት ጉዳይ ያለኝን አቋም ልንገሮት ኢህአዴግ ምርጫውን ከቻለ በትክክል ለማሸነፍ ካልቻለ ደግሞ በየምርጫ ጣቢያ ባሰማራቸው ታዛቢና አሰመራጮች አማካይኝነት የምርጫ ውጤቱን ማስለወጥ የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ እንደተዘጋጅ አውቃለው፡፡ ለዚህም ህገወጥ የሆኑቱን ተገባራት ሁሉ ከማድረግ እንደማይመለስ አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ በፍቼ ለታዛቢነት የላክናቸውን ልጆች ያደረጉትን፤ በትግራይ በአቶ ስዬ ምርጫ ጣቢያ ያሳየውን ባሕሪ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በከተማ ደግሞ የተለየ ነበር፡፡ በከተማ የተዘጋጀውን ከመከላከል አንፃር እኔ ምርጫ ክልል መቶ በመቶ በቁጥጥራችን ስር አድርገን ተወዳድረናል፡፡ በውጤት ካልተለካ በስተቀር መቶ በመቶ አልተሳካልንም፡፡ ዝርዝሩን ሌላ ጊዜ በሌላ መልክ እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡ ጠቃሚ ነው ብዬ ስለማምን፡፡ እርሶ ግን ያልተመረጡት ምርጫውን በማንኛውም መንገድ ለማሸነፍ ከቆረጠው ኢህአዴግ ጋር የሚመጥን ዝግጅት በምርጫ ክልል ስለአላደረጉ ነው የተሸነፉት፡፡ ይህንን ለማስረዳት በተወዳደሩበት ምርጫ ክልል ሰንት ታዛቢ አሰማርተዋል? ሰንቶቹ ታዛቢዎች ኢህአዴግ አሰፈራራን ብለው ጥለው ወጡ? በተወዳደሩበት ምርጫ ጣቢያ የተገኘውን ውጤት በሙሉ ቆጥረው ተቀብለዋል? በውድድሩ ወቅት ለምርጫው የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟልተው ነው የተወደሩት? (ወደ ዝርዝር አልገባም እንዳላደረጉት ሰለማውቅ)፡፡ በረከት ታሸንፋለህ ብሎኛል ብለው ምርጫ ጣቢያዎን ለዕድል ጥለው አዘርፈው አንድም ቢሆን ያሸነፈን ሰው ኢህአዴግ ነው የሰጠው ብሎ እኝኝ ማለት ምን ይባላል፡፡ ለኢህአዴግ ከኔ ይልቅ በምንም መስፈርት እርሶ እንደሚቀርቡት ማንም ያውቃል፡፡ ኢህአዴግ በሰራው ድራማ ተመርጨ ብሆን አንኳን ባለፈው ፓርላማ ዘመን ምን ምን ለኢህአዴግ እንደሰራው ማስረጃ አቅርበው አይሞግቱኝም?
የእኔን ለኢህአዴግ ቅርብ መሆን እና አለመሆን ማወቅ ከፈለጉ አልፎ አልፎ የማውጣቸውን ሁለገብ ፅሁፎች ማንበብ ነው፡፡ እነዚህ ፅሁፎች የሚቃኙበትን አሰተሳሰብ ሊረዱት ይችላሉ፡፡ የሚገርሞት ይህ አስተሳሰቤ ደግሞ ኢህአዴግ መሆንንም አጥያት አያደርገውም፡፡ ለዚህም እኮ ነው በአሰተሳሰብ እርሶ ለኢህአደግ  እንደሚቀርቡ ብናውቅም ትግሉ አሁን የርዕዮታ ዓለም ፍልስፍና ጉዳይ ሳይሆን መሰረታዊ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጉደይ ሰለሆነ ነው በመድረክ አብረን የምንሰራው፡፡ ይህ ደግሞ ሰው መሆን ብቻ በቂ ስለሆነ ነው፡፡ ነውርነት የለውም፡፡ በሀገራችን ምቹ ምዕዳር ተፈጥሮ የፖለቲካ ጫወታው የርዕዮት ዓለም ጉዳይ በሚሆንበት ወቅት፤ ለኢህአዴግ ቅርብ የሚሆኑት እርሶ ሰለሚሆኑ ኢህአዴግ በካድሬነት ባይችሉ እንኳን ለአማካሪነት የሚፈልጎት እርሶ እንደሚሆኑ አንድም ጥርጥር አይኖረኝም፡፡ ዕድሜና ጤና ከተገኘ፡፡ በኢህአዴግ መንግሰት ሚኒስትር የሆኑትና ለኢህአዴግ ፕሬዝዳንት ለመሆን የተወዳደሩት እርሶ መሆንዎን መዘንጋት የለቦትም፡፡ ቅርብ መሆንዎን ለማሳየት ብቻ ነው ይህን ያነሳሁት፡፡ እኔ ግን የኢህአዴግን ስልጣን ወድቆ ባገኝ እንዲያነሱት ከመንገር ውጭ ልመኘውና ልወስደው አልችልም፡፡ እኔና ኢህአዴግ የሚያገናኘን ሀገር እንጂ ርዕዮታለማዊ መስመር የለንም፡፡ ግልፅ ነው ብዬ ልውሰደው?
ግርማ ሠይፉ ማሩ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ከቁራና ከዳዊት የቱን ይመርጣሉ? ከተከበሩ ግርማ ሠይፉ ማሩ



አልፎ አልፎ ጠዋት የማገኛቸው የማኪያቶ ቡድን አለ፡፡ በፓርላማ ሰለነበረው ውሎ መሠረት አድርገው የግል አሰተያየት ይሰጣሉ በዚህ መሃል አንዱ ምሳሌያዊ ንግግር አደረገ ወደድኩትና ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡ ቁራ ታውቃላችሁ በተለይ መሬት ላይ በእግሯ ስትሄድ አታምርም ይህ ችግር እንዳለባት ታውቃለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእርግብ አካሄድ ይማለርካታል፡፡ አካሄዷን ለማሳመር እንደ እርግብ መሄድ ይኖርብኛል ብላ ወሰነችና ልምምድ ጀመረች፡፡ አስር ዓመት ሙሉ ቤት ዘግታ ስትለማመድ ቆይታ ሳይሳካላት ይቀርና ተስፋ በመቁረጥ አንድ ውሣኔ ላይ ትደርሳለች ቢያስጠላም በራሷ በቀድሞ አካሄድ እንደ ቁራ ለመሄድት ወስናለች፡፡የሚያሳዝነው ነገር ግን የእርግብንም ሳትለምድ የራሷም የቁራ አካሄድ ጠፋባት፡፡
የዚህ ምሳሌ መነሻ የሆኑት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ናቸው፡፡ በምክር ቤት ውስጥ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ለመምሰል ሲያደርጉ የነበረውን ሙከራ የትዝብቱ አንድ አካል ነው፡፡ በዚህ ዕይታ ሙሉ በሙሉ ባልስማማም ፍፁም ውሽት ነው ራሳቸውን ነበር የነበሩት ብዬ ልከራከር አልችልም፡፡ እኔም የሆነ ነገር ታይቶኛል፡፡ ስለዚህ ይህ ማሳሰቢያው አቶ ሀይለማሪያም መለስን ላይሆኑ ሀይለማሪያምን እንዳያጡት የተሰጠ ምክር በመሆኑ በበጎ ወስጀዋለሁ፡፡
የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ በደንብ በሚያውቁት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ላስረዳ፡፡ መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ምዕራፍ 17 ዝርዝሩን ማየት ይቻላል በአጭሩ ታሪኩ የጎሊያድና የዳዊት ነው፡፡ ንጉስ ሳኦል ዳዊት ጎልያድን ለመግጠም ይመረጥና ይልከዋል ወደ ፍልሚያው ሊገባ ሲል፤ ሳኦል ለዳዊት እንዲጠቅመው በሚል የንጉሱን ካባና ንጉሱ በጦርነት ጊዜ የሚጠቀምበትን ዋነኛ መዋጊያ የሆነ የናስ ቁር ደፋለት፤ ጥሩርም አለበ ሰው፡፡ የንጉሱን ልብስ ለብሶ መንገድ ሲጀምር አልተመቸውም አውልቁልኝ ብሎ አወለቀው፤ በማስከተልም የተሰጠውን ትጥቅ ይቅርብኝ ብሎ ወንጭፌን አምጡ አለ፡፡ ከዚያም ብዙዎቹ በዚህ አለባበስና በወንጭፍ እንዴት ጎልያድን የሚያክል ግዙፍ ሰው ለማሸነፍ እንደሚችል ሲጠየቅ ጎልያድ እንደምታዩት ትልቅ ነው (የጎልያድ ቁመት ከስድስት ክንድ በላይ ነው) ለኔ ጎልያድን መምታት ሳይሆን መሳት ነው ከባድ ይላቸዋል፡፡ ግጥሚያው ሲጀመርም ዳዊት ጎልያድን በወንጭፍ ግንባሩን ብሎ ጣለው፡፡ እንዳለውም ጎልያድን መምታት ሳይሆን ከባድ መሳት ከባድ መሆኑን አስመሰከረ፡፡ ዳዊት ያደረገው ከንጉሱ ካባ ይልቅ የራሱ ደበሎ፤ ከንጉሱ ዘመናዊ መሳሪያ ይልቅ የራሱ የሚያውቀው ወንጭፍ እንደሚሻል አሰመሰከረ፡፡ እዚህ ጋ ለአቶ ሀይለማሪያም የተላለፈው መልዕክት የንጉሱ ሌጋሲ ማስጠበቅ በሚል ሳይሆን በራሳቸው ደበሎና ወንጭፍ እንዲጠቀሙ ለማሳሰብ ነው፡፡
እነዚህ ሁለት ምሳሌዎች ለአቶ ሀይለማሪያም በጣም ጥሩምሳሌዎች ናቸው፡፡ ምርጫው እንደ ቁራዋ ሌላ ለመሆን ሞክሮ እራሳቸውንም መሆን አቅቶዋቸው ሳይሳከላቸው መቅረት ወይም እንደ ዳዊት የንጉሱን ትተው እራሳቸውን መሆን ነው፡፡ ምርጫው የግል ነው የኛ ጉዳይ መምከር ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሳቸውን እንዲሆኑ የምፈልግበት አንድ ሁለት ነጥብ ላንሳላችሁ አንድ የፕሬስ ህግ የመናገርና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የንግድ ህግ መሆኑን አናውቅም ነበር፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች በንግድ ህግ ብቻ የሚጠቀሱ ቢሆን ኖሮ በፍትሕ ብሔር ህግ እንጂ በህገመንግስት ውስጥ የሚጠቀሱ አይሆኑም ነበር፡፡ የህገ መንግሰቱን አንቀፅ 29/2 እና ሌሎችም ድንጋጌዎች እንዳይሸራረፉ መጠየቅ በንግድ ህግ እንዲታይ ማለት ተገቢ አይደለም፡፡
ነጋዴዎች የያዙትን የንግድ ቤት በሽያጭ ይተላለፍ የሚል አስተያየት ሲሰጥ ይህ ዓላማው ድሃው እንዲኖርበት ነው ማለት የእውቀት ሳይሆን ጉዳዩ ሌላ ነው ፣ ድሃው የሚኖርበት ቤትም ቢሆን ለድሃ በይዞታነት ይተላለፍ ማለት ይቻላል፡፡ በጥያቄ የቀረበላቸው ግን ነጋዴዎች እየነገዱ ያሉበትን ቤት ባለቤትነት አዛውሩና ገንዘብ ተቀበሉ፡፡ የተቀበላችሁን ገንዘብ ደግሞ ለኢንቨስትመንት አውሉት ማለት ለወዳጅ የተሰጠ ምክር ነው፡፡ ልብ ብለው ያድምጡኝ ይህ ምክር ከተቀናቃኝም ቢሆን ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ ለነገሩ ዓላማው እራሱን ችሎ የሚኖር ነጋዴንም ቢሆን በጭሰኝነት መያዝ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ ለነፃነት ስንል ጫካ ገባን የሚል ቡድን የዜጎቸን ነፃነትን ለመገደብ ምንም መንገድ እንደሚጠቀም ማሳያነው፡፡ ይህ ደግሞ ጫካ የመግባታቸው ሚስጥር ለነፃነት ነበር የሚለው ነጭ ውሽት እንደሆነ መረዳት ከበድ አይሆንም፡፡ ነፃነትን የሚያከብር ቡድን በምንም ዓይነት የሌሎችን ነፃነት በቁሳዊ ጉደይ ለመያዝ አይጥርም፡፡ ነፃነት የማያውቅ ነፃ አውጭ የሚለው የሚገልፃችሁ ይመስለኛል፡፡

Girma Seifu Minneapolis Flyer


Girma Seifu Picture 2


Girma Seifu Picture